የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መኾኑን ገለጸ።

22

ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኢትዮ ቴሌኮም ለዜጎች ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ኢትዮ ቴሌኮም በክልሉ ያለውን ዘመናዊ የፍርድ ቤት አገልግሎት በማገዝ ላሳየው ቀና ትብብር አመስግነዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለተገልጋዮች ዘመናዊ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ዋና መሥሪያ ቤቱ በዘመናዊ መልኩ እና ለተገልጋዮችም ምቹ እንዲኾን ተድርጎ እየታደሰ ነው ብለዋል።

ፍርድ ቤቶችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ ዜጎች ገንዘብ እና ጊዜያቸውን በማያባክን መልኩ ከእንግልት ነጻ ኾነው በአካባቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው ስምምነት በክልሉ ያሉትን ፍርድ ቤቶች በኔትወርክ በማገናኘት ዲጅታል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የለውጥ ሥራዎች በአካል በመመልከት ዲጅታል የፍትሕ ሥርዓቱን ለመደገፍ ላደረጉት ተነሳሽነትም አመስግነዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የሕዝብ የቀልጣፋ አገልግሎት ፍላጎት አድጓል፤ ይህንን ፍላጎት ለማቅረብ ደግሞ ዲጅታል አሠራሮችን መዘርጋት ግድ ይላል ብለዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች በዲጂታላይዜሽን አሠራር እንዲዘምኑ ኢትዮ ቴሌኮም በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአማራ ክልል የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እየሠራ ነው ያሉት ሥራ አሥፈጻሚዋ ዛሬ ደግሞ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቴክኖሎጅ በማስታጠቅ ሥርዓቱን እንዲያዘምን የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል ነው ያሉት። ዲጂታል አገልግሎት የፍትሕ ሥርዓቱን በማዘመን ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል።

ቴክኖሎጅን መጠቀም የሰው ልጅ ሕይወት አድካሚ እና አሰልች እንዳይኾንበት ያደርጋል ነው ያሉት። የፍትሕ ሥርዓቱ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው እንጂኾን ለማስቻል ተቋማትን ቴክኖሎጅ ማስታጠቅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በጋራ በመኾን ዜጎች ባሉበት አካባቢ ኾነው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል፣ አላስፈላጊ እንግልትን የሚያስቀር፣ ወጭን የሚቀንስ እና ጊዜን የሚቆጥብ ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት በትኩረት እንደሚሠራም ሥራ አሥፈጻሚዋ ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ዝርጋታው በፍጥነት ተጠናቅቆ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ ለመቀራረብ እና ለመግባባት የማይተካ ሚና አለው” መልካሙ ጸጋዬ
Next articleየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የኖርዌይ ፍትሕ ሚኒስትር ኤምሊ ኧንገር መኸልን በጽሕፈት ቤታቸው አነጋነሩ።