“የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ ለመቀራረብ እና ለመግባባት የማይተካ ሚና አለው” መልካሙ ጸጋዬ

34

ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ 16ኛው ክልል አቀፍ የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫልን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የአማራ ክልል ባለብዙ ዘርፍ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መኾኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕላዊ ትውፊቶች እና ሃይማኖቶች ያሏቸው ሕዝቦች ተፈቃቅረው፣ ተዋድደው፣ ተሳስበው እና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩበት ክልል መኾኑንም ተናግረዋል። የማንነት መገለጫ የኾኑ የሃይማኖት እና ባሕላዊ ሁነቶች እንዳሉም ገልጸዋል። ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሁነቶች ኢትዮጵያውያን በሰላም እና በአንድነት አንዲኖሩ፣ ተመሳሳይ ታሪክ እና ሥነ ልቦና እንዲያዳብሩ ያደረጉ፣ የሕዝብ አንድነት መሠረቶች የኾኑ፣ የፍቅር እና የመተሳሰሪያ ጠንካራ ገመዶች ናቸው ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ ቱባ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ቅርስነታቸውን ጠብቀው ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የአሁኑ ትውልድ የወረሳቸው ሃብቶች እንዳሉትም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ባሕሎች፣ ቀንቋዎች፣ የጥበብ ውጤቶች ሳይበረዙ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች የማንነት መገለጫ የኾኗቸውን ባሕሎቻቸውን እና የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ የባሕል ፌስቲቫል እንደሚዘጋጅ ነው የተናገሩት። ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ላለፉት ዓመታት የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫል እያዘጋጀ መምጣቱን አመላክተዋል።

የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫል ባሕልን ለማስተዋወቅ እና ለመሸጥ የጎላ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት። ፌስቲቫሉ ለመቀራረብ እና ለመግባባት የማይተካ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል። 16ኛው ክልል አቀፍ የባሕል እና የኪነጥበብ ፌስቲቫል “ድንቅ ምድር ድንቅ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ይከበራል ነው ያሉት።

በዓሉ ከጥር 07/2017 ዓ.ም እስከ 09/2017 ዓ.ም እንደሚከበርም ገልጸዋል። በበዓሉ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ እና አካባቢያቸውን የሚወክሉ የባሕል ቡድኖች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል። የአጎራባች ክልሎችም የባሕል ቡድናቸውን ይዘው እንደሚገኙ የተናገሩት ኀላፊው በዓሉ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

ፌስቲቫሉ የክልሉን ባሕል እና ኪነጥበብ እንደሚያነቃቃም ገልጸዋል። ለዘመናት የሕዝብን አንድነት ጠብቆ እና አስተሳስሮ የኖረውን እና የሚኖረውን አኩሪ ባሕል ጠብቆ እና ተንከባክቦ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ነው ያሉት።

የክልሉን ባሕል እና ኪነጥበብ በማስተዋወቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የእድሳት ሥራ ተጠናቅቆ ተመረቀ ፡፡
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መኾኑን ገለጸ።