
አዲስ አበባ: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ውጤታማ ሊያደርጓት የሚችሉ ፖሊሲዎችን እና አዋጆችን ቀርጻ እየሠራች መኾኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሀገር አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ንቅናቄን አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ መልእክታቸው 50 በመቶ የኾነው የደጋማው የሀገራችን ክፍል በአስቸጋሪ የአፈር መሸርሸር የተጋለጠ ነው ብለዋል። መንግሥትም ይህንን ችግር በመረዳት ለመፍትሔው እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ፣ የገጠር የመሬት አጠቃቀም እና አሥተዳደር አዋጅን ባለፈው ዓመት አጽድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል። የአፈር ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻር መርሐ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ የደን ሽፋንን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በየዓመቱ 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን አፈር በመሸርሸር እንደምታጣ አመላክተዋል። ባለፉት 20 ዓመታት 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። አጠቃላይ እንዲያገግም ከተደረገው መሬት 24 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኅብረተሰቡ አቅም እንዲገነባ የተደረገ ነው ብለዋል። የተሠራው ሥራ 18 ቢሊዮን ብር የገንዘብ አስተዋፅኦ ይገመታል ነው ያሉት።
ለተፈጥሮ መዛባት አስተዋጿቸው አነስተኛ ቢኾንም በጥበቃው ላይ ግን ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ያሉት አርሶአደሮች ናቸው ብለዋል። የልማት አጋሮች ይህንን ሥራ በመደገፍ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የሚያደርጉትን ጥረት በቴክኖሎጅ ሊያግዙ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የዓለም አቀፍ የግብርና ፈንድ ልማት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማዋሪ ቺቲማ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ እና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራን በመፍጠር እና በማቀናጀት ጠንካራ የተፈጥሮ አደጋን የመቋቋም ኹነትን ለመፍጠር ሚናው ትልቅ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!