
ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ቀን ከወረዳ የመጣ የዘመድ ልጅ አንድ መሥሪያ ቤት ባወጣው የሥራ ቅጥር ለመወዳደር ወደ ባሕር ዳር መጣ። አውቶቡስ መነኻሪያ ሄጄ ተቀበልኩትና ወደ ቤት ከመሄዳችን በፊት ሻይ ቡና ለማለት ወደ አንድ ካፊቴሪያ ገባን። ከመኪና እንደተቀበልኩት መንገዱ በመበላሸቱ ጉዞው ስቃይ መኾኑን እና ከታሪፍ በላይ በመክፈሉ እየተናደደ መምጣቱን አወራኝ። ”ለአንድ ቅጥር ስንት መቶ ሰው ለሚመዘገብበት ሥራ ልፋ ቢለኝ ነው” ሲልም ምሬቱን ጨመረ።
ሻይ አዝዘን እስኪመጣልን፣ ሻይ ከመጣልን በኋላ እየጠጣንም የሀገር ቤቱን እና የዘመድ ወጉን ስንጨዋወት ቆየን። ለጠጣነው ሻይ ለመክፈል ተገላገልን እና እሱ አሸንፎ አንድ መቶ ብር ሰጠ። አስተናጋጇ ብሩን ወስዳ መልሱን በመጠቅለያ ነገር ጠረጴዛችን ላይ አስቀመጠችለት። ከተመለሰለት ብር ላይ አሥር ብር ለአስተናጋጇ ጉርሻ አስቀረና ቀሪውን ጠቅልሎ ወደ ኪሱ አስገባ።
ነገር ግን ደረሰኝ አልተሰጠውም ነበርና ነገርኩት።
”ተዋቸው ባክህ” አለኝ።
”ለምን” አልኩት
”ደረሰኝ ሰጡኝ አልሰጡኝ ምን ይጠቅመኛል?”
”ሕጋዊ ግዴታህን ትወጣበታለሃ! መቼም ቤቱ የቫት ተመዝጋቢ ነው አይደል?” ስል በእርግጠኝነት ስሜት ጠየኩት።
እንደሚስማማ ጠብቄያለሁ።
”የኾነ እንደኾንስ?” አለኝ ፍርጥም እንዳለ።
”ከከፈልከው ገንዘብ ውስጥኮ 15 በመቶው መንግሥት ከአንተ እንዲሰበስቡለት ስላዘዛቸው የቆረጡብህ ነው”
”እና ወሰዱትኮ”
”ደረሰኝ ሊሰጡህ ይገባላ”
”ባይሰጡኝስ?”
”ካልሰጡህማ እንኳን የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር ተቀብለናል ሊሉ ሻይውንም እንዳልሸጡ ነውኮ የሚታሰበው”
”ተው ባክህ በዚህ ጉዳይ አንጨቃጨቅበት” አለኝ እየተሰላቸ፤ ”መንግሥት ቢወስደውስ ምን ሊጠቅመኝ?” አለ ገንዘቡ ማንም ይውሰደው ማን ግድ እንደሌለው በሚያመላክት ስሜት።
”እንዲያውም መንግሥት ከሚበላው ወገኔ ይብላው” ሲልም አከለ።
”አልገባህም ወንድማለም” አልኩት። ለዝርዝር ወሬ እየተዘጋጀሁ፤ እሱ ግን መነሳት አምሮታል።
”ቅድም ስለመጣህበት መንገድ አለመመቸት፣ ስለ ከፈልከው ገንዘብ ከተመን በላይ መኾን፣ የሥራ እድል በመጥፋቱ ለአንድ ሥራ ለመወዳደር በርካታ ሰው እንደሚሰለፍ እየዘረዘርክ ስታማርር አልነበረም?” አልኩት።
”እና ለዚህ ሕግ ለማያስከብር፣ እንድንገላታ ላደረገኝ መንግሥት ነው የምቆረቆርለት?” አለኝ በልበ ሙሉነት እና ራሱ ባመጣው ሃሳብ ረታሁት በሚል ስሜት እየተጀነነ።
”ልክ ነህ” አልኩት እውነትን ከውሸት ለይቶ መናገር ሃሳብን ለማሳመን እንደሚመች እያሰብኩ።
”ልክ ነህ፤ መንግሥት የተለያዩ ዓይነት ግብሮችን የሚሰበስበው ለልማት፣ ለሕግ ማስከበር፣ አንተ ለምትወዳደርበት ዓይነት የሥራ እድል ፈጠራ እና ለመሰል ሥራዎች በጀት ስለሚያስፈልገው ነው።
ነገር ግን ብር ከሌለው እንዴት አድርጎ ምቹ መንገድ ይሥራ? እንዴት አድርጎ የመንገድ ደኅንነት እና የትራፊክ ሕግ አስከባሪዎችን ይቅጠር?….”
”ቢቀጠሩስ መች አስከበሩት” ሲል አቋረጠኝ።
እኔም ”እኛ ስንጠየቅ እውነቱን አንናገርማ” አልኩ ፈርጠም ብየ። ”የክርክራችን መነሻኮ ከከፈልከው ገንዘብ ላይ 15 በመቶው ተጨማሪ እሴት ታክስ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ደረሰኝ ተቀበል ብሎ መንግሥት ያወጣውን ሕግ በግዴለሽነት ስለተውከው ነው” ስል ሞገትኩ።
”ባለመኪኖች አላግባብ ሲያስከፍሏችሁ ሁላችሁም በአንድ ላይ አንከፍልም ብትሉ፣ ወይም ደረሰኝ ብትጠይቁ ለሕግ አስከባሪ ከስሳችሁ አላግባብ የተወሰደባችሁን ማስመለስ ትችሉ ነበር” አልኩት።
ቀጠልኩና ”ደግሞስ ሕግን ማስከበር ለመንግሥት አካላት ብቻ የተወው ማነው? አንተ ካልጮህ ማን ይድረስልህ? ለከፈልከው ገንዘብ ደረሰኝ ተቀበል የሚል ሕግ እንዳለ እያወቅህ በቸልታ ተውኸው። ሕግ ጣስህ። አንተ ያላከበርከውን ሕግ ነጋዴ ብቻ ሊያከብርልህ አይችልም።
እንዲያውም ደረሰኝ ጠይቀህ ባይሰጡህ እንኳ አፋጥጠህ፣ ተጨቃጭቀህ ወይም ለሕግ አካል አመልክተህ መቀበል ነበረብህ” ስልም ተነተንሁ።
”ባክህ እነሱም እየተመሳጠሩ ነው የሚበሉን”
”ሕጉን አክብረን እና መብታችን በቀጥታ ሳንጠይቅ? ሁሉም ተመሳጣሪ እና ሌባ ሊኾን አይችልም”
”እንዲያውም ሕዝብ ግዴታውን አውቆ መብቱን በተባበረ ጉልበት ቢጠይቅ ሕግም ይከበራል፤ ሕገ ወጦችም የልብ ልብ አይሰማቸውም ነበር” አልኩት።
ወንድሜ እና የሱ መሰል ሰዎች ልማት፣ ሕግ መከበር፣ ምቾት እንደመፈለጋቸው ሁሉ መንግሥትም እነዚህን ነገሮች የሚያሟላበት ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አልተገነዘቡም። ቢገነዘቡም የግብርን አስፈላጊነት ያቃልላሉ።
ገንዘቡ ቢሰበሰብም ከልማት ይልቅ ለምዝበራ ይዳረጋል የሚሉም አሉ። የከፈልሁት ግብር በመንግሥት በባለሥልጣናት ከሚመዘበር ግለሰቦች ይመዝብሩት የሚል አማራጭ ያላቸውም አሉ።
ግብርን በአግባቡ በመክፈል እና ለታለመለት አካል እንዲደርስ በታማኝ ዜግነት እና በቁርጠኛነት ከተሠራ መዝባሪዎችም የማይከስሙበት ምክንያት አይኖርም። የሃቀኛ ዜጋ መብዛት ለመዝባሪዎች ምቹ አይኾንምና።
ከጓደኛዬ ጋር ከካፊቴሪያው ብንነሳም ወሬያችን ግን ቀጥሏል።
”ባክህ ሀገሪቱ አምስት አስር ተሰብስቦ አይደለም የሚያልፍላት” አለ በሌላ የመከራከሪያ አመክንዮ።
”እና ነዳጅ ይፍለቅ ወይስ ወርቅ?” ስል አሾፍኩበት።
”ሁሉም ሀገርኮ ነዳጅም ወርቅም የለውም፤ ያለውን ሀብት በሕግ እና በሥርዓት እያለማ ስለሚጠቀም እንጂ። ደግሞኮ በሃብት የተንበሻበሹትም ከዜጎቻቸውም ኾነ ከንግድ ድርጅቶቻቸው ጥብቅ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት እንደሚከተሉ ይነገራል።
አሁን ላለመረታት እንጂ የመከራከሪያ ሃሳብ አልቆበታል፤ ወይ ደግሞ ‘ይሁንልህ’ በሚል ስሜት ዝም ብሎ ማድመጥን መርጧል። እኔም በአሸናፊነት ስሜት ወሬየን ቀጠልኩ።
”ግብር በአግባቡ ካልተሰበሰበ አንተን ያንገላታህ ያረጀ መንገድ በምን ይታደስ? እላፊ ያስከፈሉህ ባለመኪኖችምኮ አንዳንዴ እውነት አላቸው፤ መንገዱ ስለተጎዳ የመኪናችን የውስጥ እቃ ይጎዳል እናም ከክፍያ ላይ ጨመርን እያሉ ነውኮ።
በመንገዱ አለመጠገን መንግሥትን አምተን እና ንቀን በግብሩም መንግሥትን አልተባበር ካልን ታዲያ ከየት አምጥቶ መንገድ ይጠግንልን? ሕግ ያስከብርልን? ነገር ግን አሁን አንድ ችግር ቢገጥመን በሰላሙ ጊዜ የናቅኸው፣ ያጣጣልከው እና ባወጣው ሕግ ያልተባበርከው መንግሥትን ፖሊስ አይናችን ማማተሩ አይቀርም” በማለት ነገሬን በምክንያት ላስረዳው ሞከርኩ።
ቢቸግረው ”አሁንስ የሻይውን አንተ በከፈልከውና የምታደርገውን ባየሁህ” አለኝ።
”የግብር ሕግ እውቀታችን እና ቁርጠኝነታችን ከዚያ ስላልደረሰ እንጂ ግብር ሲሰውር የተመለከተም መቃወም እናመክሰስ ይጠበቅበታል እና እኔም ጥፋተኛ ነኝ” አልኩት
”ከወረዳ አምጥተህ ከዚሁ አሳስረኛ!”
”እኮ ይህንን አስቤማ ለፈጸሙት ሽያጭ ያለደረሰኝ ክፍያ ሲቀበሉ እያየሁ ዝም አልኩኮ፤ እኔም አወራሁ እንጂ ጥፋተኛ ነኝ” አልኩ የጥፋቱ ተባባሪነቴን እያመንኩ። ሕጉ የምናውቀውን ያህል በተግባር ጠንካራ አይደለንም። ጥቂቶች ግብር ለሀገር ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይገነዘባሉ፤ የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈልም ይፈልጋሉ፤ ምቹ ኹኔታ ካገኙም ይከፍላሉ።
ነገር ግን እውነተኛ የዜግነት ፍላጎታቸውን በይሉንታ የሚሸበብበት ጊዜ ይኖራል። ‘ለሻይ ዋጋ አልጨቃጨቅም’፣ ‘ከዚህ ሕዝብ መሃል እንዴት በደረሰኝ ምክንያት እጣላለሁ’፣ ‘ሁልጊዜ እኔ ብቻ ተጨቃጭቄ ለውጥ አላመጣም’፣ ‘አንዳንድ ግብር ሰዋሪዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ትሥሥር ይኖራቸዋል’ እና የመሳሰሉት ሃሳቦች የግብር ቀና አመለካከታቸውን ይፈታተንባቸዋል።
የሥራ እድል ፈጠራ፣ የመንገድ እና መብራት ዝርጋታ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የሕግ መከበር፣ ሰላም፣ ፍትሕ እና መልካም አሥተዳደር መስፈንም ከሚወሰንባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በቂ በጀት መኖሩ ነው። ሕግ አክባሪ እና አስከባሪ ሕዝብ ሲኖር የመንግሥት አካላትም በኀላፊነት ስሜት እንዲሠሩ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይኾንም። በግብር ላይ ግዴለሽና አላዋቂ በኾንን ቁጥር በልማት አለመስፋፋት፣ በሕግ አለመከበር እና በሥራ አጥነት ችግር እንከበባለን። ስለዚህ እኛ የሚጠበቅብንን እንወጣ።
በተፈጠረለት ምቹ ኹኔታ ሰርቶ ሚሊየነር የኾነው ነጋዴ ከሕዝብ የሰበሰበውንም የራሱንም ግብር አመስግኖ መክፈል ይኖርበታል። ተጠቃሚው ሰውም ለከፈለው ገንዘብ ደረሰኝ በመቀበል ወደ መንግሥት ካዝና መግባት ያለበት ገንዘብ እንዲገባ ቆራጥ መኾን አለበት። ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትም ሥልጣኑን እና አሠራሮችን ተጠቅሞ ግብር በአግባቡ እንዲሰበሰብ እና ሰዋሪዎችንም የማያዳግም ቅጣት በመቅጣት ሕግ ሊያስከብር እና ሊያሰፍን ይገባል። የጥፋቱ ተባባሪ ሠራተኞችንም ባለመታገስ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ዘንድ ታማኝነት ሊኖረው ይገባል።
እንዲያ ሲኾን ግብር ለልማት ያለውን ፋይዳ በተግባር የሚገነዘብ ሕዝብ እና ከሕዝብ የተሰበሰበን ገንዘብ የማይመዘብር የመንግሥት አካል መስተጋብር ይፈጠራል። ያኔም ልማት በደጃችን ሞልቶ ይፈስሳል። ከወረዳ የመጣው ዘመዴም ለሥራ ፍለጋ የሚንከራተት ሳይኾን በአካባቢው የሥራ እድሉን ያገኘዋል፤ ወይ ራሱ ሥራ ፈጣሪ ይኾናል።
የተበላሸው መንገድም ይጠገናል። ሕዝብ ማመላለሻዎችም መንገዱ ስላልተበላሸ ከተመን በላይ የሚጠይቁበት ምክንያት አይኖርም። ቢፈልጉም የሚከፍላቸው ተሳፋሪ አያገኙም። ልንሠለጥንባቸው እና ልንሻሻልባቸው የሚያስፈልጉን ሌሎች በርካታ ዘርፎች መኖራቸው ባይካድም የግብር ሥርዓቱ የዘመነበት፣ ሥልጡን ግብር ከፋይ ሕዝብ እና ለግብር ሕግ መከበር ዘብ የሚቆም ኅብረተሰብ መፈጠር ለአንድ ሀገር ልማት እና እድገት ወሳኝ ጉዳይ ነው።
እናም ተብትበው ከያዙን በርካታ ችግሮች መካከል ስለ ግብር ጠቀሜታ ያለን ግንዛቤ አነስተኛነት፣ ቸለልተኛነት እንዲሁም ራስ ወዳድነት ጎልቶ ይታይብናል። በግብር ሥርዓታችን ላይ በመወያየት እና በመግባባት ኃላፊነታችንን በተናጠልም በጋራም መወጣት ይገባናል። ያኔ እድገታቸውን እንደምናወራላቸው እና እንደምንቀናባቸው ሀገራት ሕይወታችንም የተሻሻለ ይኾናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!