አቢሲኒያ ባንክ ለዕድለኞች ሽልማቶችን አስረከበ።

42

አዲስ አበባ: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ በ”እንሸልምዎ” መርሐ ግብር ዕድለኞች ለኾኑ ደምበኞቹ ሽልማቶችን አስረክቧል።

ባንኩ ለስድስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የ”እንሸልምዎ” መርሐ-ግብር ለባለ ዕድለኛ ደንበኞች የሽልማት ርክክብ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል። ባንኩ የሀገር ውስጥ ቁጠባን እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማበረታታት ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት የበኩሉን ሚና እየተጫዎተ እንደሚገኝ ገልጿል።

የአቢሲኒያ ባንክ የደንበኞች ዋና አሥተዳደር መኮነን ደሳለኝ ይዘንጋው ባንኩ ከየካቲት 26 እስከ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ወራት ሲያከናውነው የነበረው የ”እንሸልምዎ” መርሐ ግብር የሀገር ውስጥ ቁጠባን እና የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ የደንበኞች ማበረታቻ እንደነበር ገልጸዋል።

ለአራት ወራት ሲከናወን በቆየው መርሐ ግብርም ከ8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ 22 ሽልማቶችን ያካተተ 7 የሽልማት አይነቶች በዕጣው መካተታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በ6ኛው የ”እንሸልምዎ” መርሐ ግብር ስምንት ዕድለኞችን ከስማርት ስልክ እስክ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል መኪና አስረክቧል።

አቢሲንያ ባንክ ለደንበኞች ተደራሽ በመኾን በዲጂታል ቴክኖሎጂ፤ በሠለጠነ የሠው ኀይል፣ በቀልጣፋ የአሠራር ሂደት በመታገዝ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየሠራ መኾኑም ተመላክቷል። ባንኩ የዲጂታል ቁጠባ እና ብድር፣ ንክኪ አልባ የክፍያ ካርድ፣ ዘመናዊ የሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ ሌሎች ደንበኛ ተኮር በኾኑ አገልግሎቶች ተመራጭ ኾኖ ለመቀጠል በትጋት እየሠራ መኾኑም ተገልጿል።

ጥራት ያለው የባንክ አገልግሎት በመስጠት በሁሉም መለኪያዎች ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ ሀገራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር
Next articleየዘንድሮውን የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠራ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።