“የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር

21

ደብረ ማርቆስ: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ማኅበረሰቡ ከጸጥታ አካሉ ጋር በመቀናጀት የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። የጥምቀት በዓል በክርስተና ዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 በድምቀት ይከበራል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ በዓሉ በአደባባይ የሚከበር በመኾኑ” ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ” ብለዋል ፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በከተማ አሥተዳደሩ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውንም ተናግረዋል።

በዕለቱ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ ኀይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ በስምሪት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኮማንደር ቢምረው ማኅበረሰቡ የጸጥታ ስጋት የሆኑ ምልክቶችን ሲመለከት ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ ጥቆማ እንዲሰጥም አሳስበዋል።

በበዓል ወቅት ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የቡድን ጸብ፣ቤት ሰብሮ ዝርፊያ እና ተያያዥ የስርቆት ወንጀሎች ሊፈጸሙ ስለሚች ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅ እና ከወንጀል ድርጊቶች መራቅ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከጸጥታ አካሉ ጋር በመቀናጀት የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባሕል ተቋም በማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቢጂአይ ኢትዮጵያ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባውን መዋለ ህፃናት ትምህርት ቤት አስመረቀ።
Next articleአቢሲኒያ ባንክ ለዕድለኞች ሽልማቶችን አስረከበ።