
ደሴ: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤቱ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከማኅበራዊ ኀላፊነት ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። ቢጂአይ ኢትዮጵያ በኮምቦልቻ የማኅበረሰብ ልማት እና የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ያለውን አጋርነት የሚያንፀባርቅ መኾኑ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የተማሪ ወላጆች ከዚህ በፊት ትምህርት ቤቱ ለህፃናት ምቹ እንዳልነበር አስታውሰው አሁን ግን ደረጃውን የጠበቀ መዋለ ህፃናት በመገንባቱ ደስተኛ መኾናቸውን እና ግንባታውን ላከናወነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ መንግሥቱ አበበ በከተማዋ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት የትምህርቱን ዘርፍ ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ቢጂአይ ኢትዮጵያ የመማሪያ ክፍሎችን እና ሙሉ ቁሳቁስ በማሟላት ለኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስረክቧል ብለዋል። ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው እና ጥያቄያቸውን ተቀብለን የቦታ ርክክብ አድርገናልም ብለዋል መምሪያ ኃላፊው።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ገልጸው ቢጂአይ ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኸርቬ ሚልሃድ “ይህ ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ እና ለማኅበረሰቡ በማስረከባችን በግሌም ኾነ በኩባንያው ስም ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል::
“በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለዘላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት እና በምንሠራባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት ያጎላል” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሠልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!