
ሰቆጣ: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያስገነቧቸውን መኖሪያ ቤቶች አጠናቅቀው ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል። ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማቱ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰቆጣ ከተማ ችግኝ በመትከል የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ተወካይ እና የፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ ጣሂር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱ በየዓመቱ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሀገሪቱ በተለያዩ ከተሞች ለአቅመ ደካሞች ቤት ሠርተው እንደሚያስረክቡ እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱ በ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ በሰቆጣ ከተማ ለአቅመ ደካሞች 10 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀመራቸውን አስታውሰዋል። የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቅቀው ዛሬ ለተጠቃሚዎች ርክክብ መደረጉን አስታውቀዋል። የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ያካተተ ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክሮ በመቀጠል ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።
የዋግ ኽምረ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፈው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 138 ወገኖች የአዲስ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ጥገና መከናወኑን አስታውሰዋል። የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማትም በሰቆጣ ከተማ 10 የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተው በማስረከባቸው አመሥግነዋል። ሌሎች ተቋማትም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን የማገዝ ባሕል ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ተቋማት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ሰው ተኮር ተግባራት እያከናወኑ ነው “ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ናቸው። የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የገነቧቸው ቤቶች የዚሁ አካል መኾናቸውን ተናግረዋል። በ10 የመኖሪያ ቤቶች 33 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ መኾናቸውን አስታውቀዋል ።
የመኖሪያ ቤቶቹን ከተረከቡት መካከል አቶ አባስ ብርሃኑ እና ወይዘሮ እልፍነሽ ታደሰ በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል ። ኢዜአ እንደዘገበው መኖሪያ ቤቶችን ከቁሳቁስ ጋር በመረከባቸው የተሻለ ሕይዎት እንዲመሩ እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል ። ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱም ምሥጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!