
ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶችንና እና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በለውጡ ዓመታት በተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ዕዳ ከሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለውን ድርሻ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። መንግሥት ከለውጡ በፊት የነበሩ የሥርዓትና እና መዋቅራዊ ችግሮችን ለማስተካከል አዲስ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ የፖሊሲ ዕይታ መከተሉን ተናግረዋል።
ይህ የልማት ፖሊሲ ዕይታ ብዝኃ ዘርፍን ያማከለ፣ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ያደረገ እና አካታች ሥርዓትን ያለመ መኾኑን ጠቅሰዋል። ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ እኩል የእድገት ምንጭ እንዲኾኑ ትኩረት መሰጠቱን እና የኢኮኖሚ ተዋንያን ሚዛን መጓደል እንዲስተካከል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ይዞት የቆየውን ጉልህ ሚና ወደ ግሉ ዘርፍ የማሸጋገር ሥራ መከናወኑንም አመላክተዋል።
የልማት ፖሊሲዎቹ የዘመናት ችግር ኾኖ የቆየውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት ግብ መያዛቸውንም አስረድተዋል፡፡ በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተተገበረው ፖሊሲ ኢኮኖሚውን ማዘመን እና ለውድድር ክፍት ማድረግ ላይ መጠነ ሰፊ ሪፎርም መደረጉን ነው ያነሱት። ለዚህም የንግድ ሕጉን እና የኢንቨስትመንት አዋጁን ጨምሮ ከ80 በላይ ሕግጋት መቀየራቸውን ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ የአገልግሎት፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንትን ምኅዳርን ያሻሻሉ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ እና ትርፋማ ከማድረግ ባሻገርም በአዲሱ የፖሊሲ ዕይታ ለዓመታት ለግሉ ዘርፍ ዝግ የነበሩ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ግዙፍ ድርጅቶች ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመንግሥት ገቢን ከማሳደግ፣ የወጭ አሥተዳደርን ከማስተካከል፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ የፕሮጀክት ትግበራ እና አፈጻጸምን ከማሻሻል፣ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ከማሸጋገር አንጻር ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም የመንግሥት ገቢ ከለውጡ በፊት ከነበረበት በብዙ እጥፍ ማደጉን በማሳያነት አንስተዋል። ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ በዕዳ ቀንበር እንድትማቅቅ ተደርጋ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህንን ለማስተካከል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምንም ዓይነት የንግድ ብድር ባለመፈጸም፣ ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ በማድረግ እና ብድርን በከፍተኛ ሁኔታ በመክፈል የዕዳ ጫናውን ማቃለል ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለባት የዕዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ 13 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት። ከለውጡ በፊት ከ30 በመቶ በላይ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መኾኑንም አስታውቀዋል። ኢዜአ እንደዘገበው የውጭ ምንዛሬ አሥተዳደር፣ ገቢ፣ የወርቅ እና የቡና የውጭ ገበያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።
አሁን ላይ ባንኮች ከሚሸጡት የውጭ ምንዛሬ ይልቅ የሚገዙት ከፍተኛ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል። የብሔራዊ ተቀማጭ መጠን 200 በመቶ ማደጉን የገለጹት ሚኒስትሯ የኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ መፈታቱንም ነው ያነሱት። ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግሥት ለደመወዝ፣ ለነዳጅ፣ ለመድኃኒት ፣ ለሴፍትኔት እና ሌሎች ድጎማዎች ከ400 ቢሊዮን ያላነሰ በጀት መመደቡን ገልጸዋል።
መንግሥት የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ቢያስቀጥልም በቅርቡ የዓለም የነዳጅ ዋጋን እና የውጭ ምንዛሬ ለውጡን መሠረት በማድረግ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉን ጠቁመዋል። አሁንም ኢትዮጵያ ነዳጅን ከዓለም ገበያ ከ20 እስከ 26 ብር ቅናሽ በማድረግ እየሸጠች እና እየደጎመች መኾኗን ነው ያስታወቁት።
መንግሥት ድኃ ተኮር ፖሊሲ የሚከተል በመኾኑ ድጎማዎቹን ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ዲጅታላይዝ ማድረግ፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠር እና ነዳጅ በአግባቡ ለተጠቃሚዎቹ መድረሱን ማረጋገጥ ላይ አዳዲስ አሠራሮች እንደሚተገበሩ አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!