የገቢ ግብር አዋጁ ምን ይላል?

321

ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም ( አሚኮ) ግብር መንግሥት በሕግ እና ደንብ ላይ ተመስርቶ ከሕዝብ እና ከድርጅቶች ገንዘብ የሚያገኝበት ነው። ዜጎች በመነገድ፣ ቤት እና ንብረት በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ እና በሌሎች የገቢ ማግኛ መንገዶች ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው መሠረት ግብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በገቢ ግብር አዋጁ 240/2008 0/2-14 ድረስ በግልጽ ተቀምጧል ።

ግብር ግብር ከፋዮች ለመንግሥት በግዴታ ክፍያ የሚፈጽሙበት መንገድ ወይም ሥርዓት ነው። በአንጻሩ መንግሥት ለኅብረተሰቡ በለውጡ ወይም በምትኩ በቀጥታ ሳይኾን በተዘዋዋሪ ልዩነት ሳይፈጥር ለሚያቀርበው አገልግሎት እና መሠረተ ልማቶች የሚያውለው ገንዘብ እንደኾነም ተገልጿል።
ግብር ከእያንዳንዱ ግለሰብ የየዕለት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ጠቀሜታዎቹም ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡

ለልማት፣ ለማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት፣ ለባሕል እድገት፣ ለሀገር ደኅንነት፣ ለፍትሕ እና መልካም አሥተዳደር መስፈን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ሀገርን ከጠላት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ባንድም በሌላ መንገድ ግብር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። ዜጎች በሰላም ወጥተው፣ በሰላም ሠርተው እና ውለው ለመግባት፣ ደኅንነታቸው እና ሰላማቸውን ለመጠበቅ፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ መንገዶችን፣ የኀይል አቅርቦቶችን ለማስፋፋት፣ ምጣኔ ሃብትን ለማነቃቃት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ ልማትን ለማፋጠን፣ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት፣ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የኾነ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ እና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ገንዘብ የሚገኘው ከግብር ነው፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ባለሙያ ባንቻየሁ አቤ ግብር ወይም ታክስ ለዜግነት የሚከፈል ዋጋ ነው ብለዋል። እንደ ባለሙያዋ ገለጻ “ግብር መክፈል ግዴታ ብቻ ሳይኾን ብሔራዊ ኩራትም ነው”። የሰው ልጆች ለመኖር እና ለመተንፈስ ሳንባ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለአንድ ሀገር ሕልውናም ግብር አስፈላጊ ነው ይላሉ። በዜጎች መካከል ያለውን የሃብት ተጠቃሚነት ፍትሐዊ ለማድረግ ግብር ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።

የመንግሥትም ሕልውና የሚረጋገጠው ለወከለው ሕዝብ ተገቢ የኾነ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ አገልግሎትን ማሟላት ሲችል ነው ያሉት ባለሙያዋ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ግብር ነው ብለዋል። ሀገር የተረጋጋ ኢኮኖሚ የሚኖረው ፍትሐዊ የግብር ሥርዓት ሲኖር መኾኑንም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ የሚያነሳውን ጥያቄ መመለስ የሚቻልበት ብቸኛው አማራጭ ግብር ነው ብለዋል። ያለ ግብር የሚመለስ ጥያቄ እንደማይኖርም ገልጸዋል። ከሀገራት ጋር ለመወዳደር ግብር አማራጭ የሌለው ግዴታ ስለመኾኑም አንስተዋል።

በታክስ አሥተዳደር አዋጅ 241/2008 ዓ.ም ላይ የታክስ ግዴታ አለመወጣትን እና ተጠያቂነቱን በሁለት ከፍሎች ያየዋል ነው ያሉት። የወንጀል ተጠያቂነትን እና የአሥተዳደራዊ ተጠያቂነት በሚል። አሥተዳደራዊ ተጠያቂነትን በተመለከተ አዋጅ 241/2008 አንቀጽ 48 ላይ የታክስ ግዴታን ባለመወጣት በክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን ትዕዛዝ ድርጅቱን የማሸግ መብት እንዳለው አስቀምጧል።

እንደየተጠያቂነቱ ቅለት እና ክብደት ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ሕጉ ይደነግጋል ነው ያሉት። አንድ ደረሠኝ መቁረጥ የነበረበት አካል ደረሠኝ ሳይቆርጥ ግብይት ሲፈጽም የተገኘ እንደኾነ እስከ 50 ሺህ ብር ድረስ አሥተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበትም ሕጉ ያስቀምጣል ብለዋል።
በሌላ መንገድ መክፈል ያለበትን ግብር ላለመክፈል ኾን ብሎ አሳንሶ በመንገር ለማጭበርበር የሞከረ እንደኾነ በልዩነት የታክስ መጠን ተሰልቶ 10 በመቶ እንደሚቀጣ ገልጸዋል።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ የወንጀል ቅጣት የሚባለው ደግሞ በአንቀጽ 119 ላይ ከደረሠኝ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ዘርዝሮ አስቀምጧቸዋል። ማንኛውም ደረሠኝ መስጠት ያለበት ታክስ ከፋይ ያለ ደረሰኝ ግብይት ያከናወነ እንደኾነ ከ25 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ድረስ በጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል ብለዋል። አዋጁ የገንዘብ ብቻ ሳይኾን የእስራት መቀጫንም ያስቀመጠ መኾኑን አስገንዝበዋል።

ግብር ከፋዩ የሽያጭ መጠኑን ለግብር አስከፋይ መሥሪያ ቤቱ በትክክል ማሳወቅ እንዳለበት ይደነግጋል ነው ያሉት። ይህ ሳይኾን ቀርቶ ግብርን ለማጭበርበር የሽያጭ መጠኑን አሳንሶ ያሳወቀ እንደኾነ ከ100 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት ድረስ እንደሚቀጣ አዋጁ አስቀምጧል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ሳይፈቅድ የታክስ ደረሰኝ ያተመ እና ሳይፈቀድለት ሢሠራ የተገኘ ከኾነም በአዋጁ መሠረት ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ የገንዘብ ቅጣት እና ከሁለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት ድረስ ጽኑ እስራት ይቀጣል ነው ያሉት። የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይመዘገብ የታክስ ደረሰኝ የሚሰጥ ግብር ከፋይ ከተገኘ በባለ ሥልጣኑ ፈቃድ ሳይሰጠው 200 ሺህ ብር ቅጣት እና ከሰባት ዓመት እስከ አስር ዓመት ድረስ ጽኑ እስራትንም ያዝዛል ብለዋል።

አሁን ተግባር ላይ ባለው አዋጅ መሠረት አንቀጽ 124 ላይ ማንኛውም ሰው ታክስን ለመሰወር በማሰብ ገቢውን የደበቀ እንደኾነ፣ የታክስ ማስታወቂያውን ያላቀረበ ወይም ታክሱን ያልከፈለ እንደኾነ ከ100 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር ድረስ እና ከሦስት ዓመት አስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ድረስ እንደሚያስቀጣ ተናግረዋል።

ለአብነት ከተነሱት ባሻገር እንደየ ወንጀሉ ስፋት እና ጥልቀት ተጠያቂነቱን አዋጁ ዘርዝሮ አስቀምጦታል ነው ያሉት። ታክሱን በሚሠበሥበው አካል ላይም በተጨባጭ የተሠጠውን ኀላፊነት ወደ ጎን ትቶ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሲሞክር የተገኘ እንደኾነ ገቢ ሠብሣቢ ተቋሙ የማጣራት እና ለሕግ የማቅረብ ኀላፊነት እንዳለበትም ጠቅሰዋል። ተቋሙ የራሱ መመሪያ እና ሕግን መሠረት አድርጎ እርምት እንዲወሰድ ያደርጋል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ ግዴታውን ማወቅ እና ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል። ግብር ካልተሠበሠበ ልማት አይታሰብም፣ ዕድገትም አይመጣም፣ የሕዝብ ጥያቄም አይመለስም ነው ያሉት። ሕጉን መሠረት አድርጎ ግዴታን መወጣት ላይ የሚቀሩ ተግባራት እንዳሉም ጠቁመዋል። አስከፋይ መስሪያ ቤቱም ለግብር ከፋዩ ተገቢውን ክብር ሰጥቶ ማስተናገድ፣ ግንዛቤን ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ 41ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች፦
Next articleከሰላም ማጽናት ጎን ለጎን ሕዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ኀላፊነት በመልካም ሙያዊ ሥነ ምግባር ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን የብልጽግና ፓርቲ አባላት ገለጹ።