
ጎንደር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪካዊቷ እና ጥንታዊቷ የጎንደር ከተማ ደምቃ እና አሸብርቃ የጥምቀት እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች። ነዋሪዎቿም የጥምቀትን ገጸ በረከት ለመቀበል እና የሩቅ ዘመድን በደስታ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው። በእንግዳ ተቀባይነት እሴት እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በልዩ ትኩረት እየተሠራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የጎንደርን ታሪክ እና ሕያው የታሪክ መለያዎቿን በሚመጥን መልኩ እየተሠራ መኾኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ለከተማዋ ውበት ልዩ ድምቀት መስጠቱንም ተናግረዋል።
ሁሉም ማኅበረሰብ ለከተማው ውበት፣ የቱሪዝም እና የልማት አምባሳደር በመኾን በዓሉ በድምቀት እንዲከበር እና እንግዶችም ተደስተው ወደመጡበት አካባቢ በሰላም እንዲመለሱ የጎንደር ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ልዕልና አበበ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በደመቀ መልኩ እንዲከበር ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የመስተንግዶ እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የጎንደርን እሴት እና መልካም ገጽታ በሚገነባ መልኩ እንዲኾኑ መሠራቱንም ተወካይ ኀላፊው ተናግረዋል።
ከበዓሉ መከበር ጋር ተያይዞ የከተማዋን የቱሪዝም ዘርፍ የሚያሳድጉ እና የሚያደምቁ የተለያዩ ኹነቶች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
