“5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሥነ ሕይወታዊ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ይሸፈናል” ግብርና ሚኒስቴር

55

አዲስ አበባ: ጥር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሃብት ልማት በተሠሩ ተግባራት የተገኙ ስኬቶችን እና በነገው ዕለት በሳይንስ ሙዚየም የሚካሄደውን ሀገር ዓቀፍ የተፈጥሮ ሐብት ሲምፖዚየም አስመልክቶ ግብርና ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ወልደየስ (ፕ.ር) በመግለጫቸው በደን መጨፍጨፍ ምክንያት የተራቆቱ አካባቢዎች ሀገሪቱን ለምግብ ዋስትና እጥረት እና ለአየር ንብረት ለውጥ አጋልጧት ነበር ብለዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም ባለፉት ስድስት ዓመታት በዘለቀው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

“በዚህ ዓመትም 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሥነ ሕይወታዊ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እንደሚሸፈን” ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። የተጎዱ ተፋሰሶችን እንዲያገግሙ ለማድረግ 600 ሺህ ሄክታር መሬት ከንክኪ በጸዳ መልኩ ይለማል ነው ያሉት። እስከ አሁን በተከናወነው ሥራም 33 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልሶ እንዲያገግም መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ 21 ነጥብ 6 ሚሊዮኑ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የለማ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። በነገው ዕለት በሳይንስ ሙዚየም የሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ሲምፖዚየምም እንደ ሀገር በዘርፉ የተገኙ ስኬቶችን በማሳየት ጥልቅ ትንታኔ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል። በሲምፖዚየሙ የክልል የሚመለከታቸው አካላት፣ አርሶ አደሮች እና ምሁራን ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

የ2017 ዓ.ም ሀገር ዓቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ እንደሚደረግም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርት እና ሥልጠና መሠረታዊ ድርጅት የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
Next article“እንግዶችን ለመቀበል ዝግጁ ነን” የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች