“የገበያ ማዕከላቱ የግብይት ሰንሰለቱን ያሳጥራሉ” ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር)

53

ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) የንግድ እና የገበያ ልማት ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በአጠረ የግብይት ሰንሰለት፣ ሕጋዊ የምርት እና አገልግሎትን በማሳለጥ የኑሮ ውድነትን ማቅለል አንደኛው ተግባሩ መኾኑን ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ግብይትን ማሳለጥ፣ ዋጋን ማረጋጋት፣ ሸማቹ ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲኾን የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ሸማች እና አምራችን የሚያገናኙ በስምንት ታላላቅ ከተሞች ላይ የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የገበያ ማዕከላቱ ሲጠናቀቁ በቀጥታ ሸማች እና አምራችን እንደሚያገናኙ ገልጸዋል።

የገበያ ማዕከላቱ የግብይት ሰንሰለቱን ያሳጥራሉ፣ ደላሎች በመካከል እንዳይገቡ ያደርጋሉ ነው ያሉት። ዋጋንም ያረጋጋሉ ብለዋል። በሌሎች ከተሞችም 75 የሚኾኑ የገበያ ማዕከላት እንዲገነቡ መግባባት መፈጠሩን የተናገሩት ኀላፊው በ50ዎቹ የማዕከላቱን መገንቢያ ቦታ መረከባቸውን ነው የገለጹት።
ከተሞች ሃብት በማሠባሠብ የሚገነቧቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የገበያ ማዕከላት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። የገበያ ሰንሰለቱ በአጠረ ቁጥር የዋጋ ንረቱም እንደሚቀንስ ገልጸዋል። ግብይት ከደላላ ነጻ የኾነ ሥራ እንደሚፈልግም ገልጸዋል።ጊዜያዊ የበዓል ገበያዎችን አቋቁመው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የቆዳ ምርት ላይ የሚነሳውን ጥያቄ ለመፍታት 33 የቆዳ ማዘጋጃ መጋዘኖችን እንዲገነቡ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

የመሠረተ ልማትን ማሟላት የግብይት ሥርዓቱን እንደሚያሻሽለው ነው ያመላከቱት። የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር መሥራታቸውንም ተናግረዋል። የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና የዩኔየኖችን አቅም ለማጠናከር 960 ሚሊዮን ብር እንዲመደብ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት። በንግድ ተዋናያኖች መካከል ትስስር መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ምርታማነትን ማሳደግ እንደተጠበቀ ኾኖ የተገኘውን ምርት በአግባቡ ማስተናገድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ምርትን በአግባቡ በማዳረስ በኩል የተሻለ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ነገር ግን አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።

የኑሮ ውድነት በተሻለ መልኩ መረጋጋት እየታየበት መኾኑንም ተናግረዋል። የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ ጋር በትስስር እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የምርት ዓይነቶች ቀድመው እንዲገቡ እያደረጉ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተደረገው ቁጥጥር ከ55 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ሕግን ተላልፈው ተገኝተዋል” ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየትምህርት እና ሥልጠና መሠረታዊ ድርጅት የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።