
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) የንግድ እና የገበያ ልማት ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ባለፉት ወራት የተቋሙን የመፈጸም አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸውን ተናግረዋል። በንግድ እና ገበያ ልማት ዘርፉ አዳዲስ ሃሳቦችን መጨመራቸውንም ተናግረዋል።
ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ሥልጠና መሥጠታቸውንም ገልጸዋል። የንግድ ምዝገባ እና እድሳት አገልግሎትን፣ የነዳጅ ሽያጭ መፈጸሚያን በቴክኖሎጂ ታግዘው መሥራታቸውን ነው የተናገሩት። የምርት ትሥሥር የሚፈጸምበት ቴክኖሎጂ አስለምተው ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አሠራሮችን ዘርግተው እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ከቀረቡ 4 ሺህ 167 ቅሬታዎች መካከል 4 ሺህ 159 ቅሬታዎች መፈታታቸውን ነው የገለጹት። ቢሮው ለሥራ የተመቸ እንዲኾን የማድረግ ሥራ ሌላው በትኩረት የተሠራበት ጉዳይ መኾኑን ነው ያነሱት። በሠራተኞቻቸው ላይ መልካም ለውጦች መታየታቸውን ነው የተናገሩት ኀላፊው አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። የንግድ መሠረቱን ለማሥፋት የነጋዴ ቁጥር መጨመራቸውን ገልጸዋል።
በገበያው ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ለሚችሉ ነጋዴዎች ፈቃድ መሥጠታቸውን ተናግረዋል። በስድስት ወራት ውስጥ ለ53 ሺህ አዳዲስ ነጋዴዎች ፈቃድ ሰጥተው ወደ ሥራ ማስገባታቸውን ነው የገለጹት። ለነባሮቹም የፈቃድ እድሳት መሥራታቸውን ነው ያመላከቱት። በስድስት ወራት ውስጥ 332 ሺህ ደምበኞች የኦንላይን አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። አገልግሎትን ከንክኪ የጸዳ የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ሕገ ወጥነትን መከላከል እና የሸማቹን መብት ማስከበር በትኩረት እንደተሠራበት ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሩ የንግድ ሥርዓቱን እንደረበሸው የተናገሩት ኀላፊው የጸጥታ ችግር ሲፈጠር ነጻ የምርት እንቅስቃሴ አይኖርም፣ የምርት እጥረት ያጋጥማል፣ በአቋራጭ ለመክበር የሚሞክረው ይበዛል ነው ያሉት።
በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነው ሕገ ወጥነትን የመከላከል እና ርምጃ የመውሰድ ሥራ መሥራታቸውን ነው የተናገሩት። ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የነጋዴዎችን ፕሮፋይል የማዘጋጀት ሥራ በመሥራት ቁጥጥር ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በቁጥጥሩ ነጋዴው ፈቃድ ስለመኖሩ፣ ጥራት ያለው ምርት እያቀረበ መኾኑን፣ ጊዜው ያለፈበት ምርት እንዳይቀርብ፣ የመሸጫ ዋጋውን የሚለጥፍ እና በደረሰኝ የሚሸጥ መኾኑን፣ የመለኪያ መሣሪያውን ትክክለኛነት እንደሚያረጋግጡ ነው የተናገሩት። ለነጋዴዎች በተዘጋጀው ፕሮፋይል መሠረት ቁጥጥር እንደሚደረግም ገልጸዋል።
መረጃ ላይ የተመሠረተ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። 55 ሺህ 454 ነጋዴዎች በተደረገው ቁጥጥር ሕግን ተላልፈው መገኘታቸውን ገልጸዋል። ሕግ ተላልፈው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል። በሕገወጥ መንገድ የሰብል ምርት እና ነዳጅ ሲዘዋወር መገኘቱንም ገልጸዋል።
10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ምርት እንዲወገድ መደረጉንም ተናግረዋል።
የነዳጅ ቁጥጥር እና ጊዜው ያለፈበት ምርት ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውንም አስታውቀዋል። የጸጥታው ችግር የንግድ ሥርዓቱን ለመቆጣጠር ፈተና እንደኾነባቸውም ተናግረዋል። ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ከማደያ ከቀዱ በኋላ በጀሪካን ገልብጠው በሕገወጥ መንገድ ይሸጣሉ፣ ሌላ ማደያ ሄደው ደግሞ እንደሚቀዱ ነው የተናገሩት። ይህ ደግሞ ቁጥጥሩን ውስብስብ እንዲኾን አድርጎታል ነው ያሉት። በተደረገው ቁጥጥር 250 ሺህ ሊትር ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ መያዙን ነው የተናገሩት። ሕገወጥ የነዳጅ ሽያጮችን ለመቆጣጠር አንድ ተሽከርካሪ በቀን ምን ያክል ሊጠቀም ይችላል የሚለውን በመለየት እየሰጡ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የአሠራር ሥርዓቱን የሚጥሱ የማደያ ባለሙያዎች መገኘታቸውንም ተናግረዋል። ነዳጅ በበርሚል ስጡን እያሉ ያልተገባ ሽርክና የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ቤንዚን ቅድሚያ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ለከተማ ትራንስፖርትም ትኩረት አድርገው መሥጠታቸውን ነው የተናገሩት። ከንግድ ሥርዓቱ የሚወጣ ማደያ ላይ ጠበቅ ያለ ርምጃ መውሰዳቸውንም ገልጸዋል። ሕገወጥነትን ከምንጩ ለመግታት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!