በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ልዩ ተወካይ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ መግለጫን አደነቁ።

44

ባሕር ዳር: ጥር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ልዩ ተወካይ እና በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ኀላፊ አምባሳደር ሞሐመድ ኤል አሚን የሱፍ የኢትዮጵ እና ሶማሊያን የጋራ መግለጫ መቀበላቸውን አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ የጋራ ጥቅሞቻቸው በኾኑ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ከትናንት በስቲያ ተወያይተዋል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራትን ወንድማማች ሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ ተመላክቷል። ሀገራቱ የነበራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ወደነበረበት ለመመለስ እና ለማጠናከር መስማማታቸውም ይታወቃል።

የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ፣ በትብብር ለመምራት እና ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮቻቸውን ለመፈጸምም ባለብዙ ወገን እና ቀጣናዊ ፎረም እንደሚያስፈልጋቸው በወቅቱ መክረዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ስምምነቱን አድንቆ ኢኮኖሚያዊ ውኅደትን ለማጎልበት፣ ለዲፕሎማሲያዊ ትስስር እና ለቀጣናዊ መረጋጋት ብሎም ለጋራ ብልጽግና አስተዋጽኦው የጎላ መኾኑን ገልጿል።

ስምምነቱን ከሶማሊያ ሕዝብ ፍላጎት እና ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የበለፀገች አፍሪካ ራዕይ ጋር በማጣጣም የሶማሊያን የሰላም ጥረቶች እና ቀጣናዊ አጋርነቶችን ለመደገፍ ተልዕኮው ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ ቀጣናዊ መረጋጋት ዕውን እንዲሆን ሁለቱ ሀገራት መተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸውም አመላክቷል፡፡

ቀጣናዊ ግንኙነትን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለማሳደግ እና ዕድገት ለማምጣት የተቀናጀ ጥረትን በማጠናከር በትብብር መሥራት እንደሚገባም መሪዎቹ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ በሀገራቱ መካከል ያለውን የደኅንነት ዘርፍ ትብብር ማስቀጠልና ማጠናከር እንደሚገባም መወያየታቸውን የጋራ አቋም መግለጫቸው ያመላክታል፡፡

የሀገራቱ የጸጥታ አካላት ትብብራቸውን በማጠናከር በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መሥራት እንደሚገባቸው መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በሁለቱ ሀገራት መካከል ማጠናከር እንደሚገባ የመከሩ ሲሆን÷ ንግድን እና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማሳደግ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

የአንካራ ስምምነትን በቁርጠኝነት በመፈጸም ወዳጅነትና ትብብርን ለማጠናከር መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በስምምነቱ መሰረት የተቀመጠውን የቴክኒክ ስምምነት ለመፈጸም መግባባት ላይ ተደርሷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ በፈተናዎች ውስጥ ኾኖም ውጤቶችን አስመዝግቧል” አቶ ሲሳይ ዳምጤ
Next article“በተደረገው ቁጥጥር ከ55 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ሕግን ተላልፈው ተገኝተዋል” ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር)