
ባሕር ዳር: ጥር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመሬት እና ማዕድን የብልጽግና ፓርቲ መሠረታዊ ድርጅት አባላት 2ኛውን የቅድመ መደበኛ ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄዱ ነው። የመሬት እና ማዕድን መሠረታዊ ድርጅት ሠብሣቢ እና የመሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በፈተናዎች ውስጥ ኾኖ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
በለውጡ ማግስት እና ለውጡን ተከትሎም አበረታች ውጤቶችን አሳክቷል ያሉት አቶ ሲሳይ በተለይ በፖለቲካ ረገድ በሁሉም ደረጃ የጠራ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ አድርጓል ብለዋል። ብልጽግና ኢትዮጵያን ከብተና የታደገ ፓርቲ ነው ያሉት ሠብሣቢው ለውጡን ተከትሎ በፈተና የተወለደው ብልጽግና ፈተናዎችን መቋቋም የቻለ እንደኾነም አንስተዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንዳትቀጥል እና ለውጡ እንዲቀለበስ አቅደው የሚሰሩ ቢኖሩ በተሠራው ጠንካራ የፓለቲካ ሥራ አንድ ኀብረ ብሔራዊ ፓርቲ በመመሥረቱ ብሎም ወንድማማችነት በመስፈኑ ሀገሪቱን ከጉስቁልና ማውጣት የቻለ ፓርቲ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ሀገርን የሚያሻግር እና ለውጡን የሚያስቀጥል ሥራ አከናውኗል ያሉት አቶ ሲሳይ የአቅም ግንባታ ሥራዎችንም አከናውኗል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ የተሰጠው ሥልጠና የአስተሳሰብ አንድነትን ማምጣቱን ሠብሣቢው ተናግረዋል። አባላቱም የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነት እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል። ፓርቲው ሁሉም ክልሎች እኩል እንዲሠሩ ከማድረጉ ባለፈ የተሻለ አፈጻጸም እና ልምድ ያላቸው ክልሎች ደግሞ ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ጥሩ የእርስ በእርስ መማማር የተገኘበት እንደ ነበር አስታውሰዋል።
“የፓርቲው አባል እና ሕዝቡ በፓርቲው ላይ የጠራ ዕምነት እንዲያሳድሩ ተደርጓል” ያሉት አቶ ሲሳይ አዎንታዊ መነሳሳት እና ቁጭትም እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል። ከኢኮኖሚ ጉዳዮች አኳያም ፓርቲው የሃብት ፈጠራ እንዲኖር እና የምጣኔ ሃብት ሥብራትን ለመጠገን መሠራቱን አቶ ሲሳይ ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሸቲቮች አተገባበር የተሳኩ እንዲኾኑ ፓርቲው የተሻሉ ተግባራት መፈጸሙን ሠብሣቢው ተናግረዋል። በሁሉም አካባቢ ተቋማት ሪፎርም ውስጥ እንዲገቡ ውጤታማ ሥራዎች ማከናዎኑንም ጠቁመዋል። በዲፕሎማሲው ረገድ ሀገሪቱ ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላም አብሮ የመልማት ድል ተገኝቷል ነው ያሉት አቶ ሲሳይ። የሕዳሴውን ግድብ በምሳሌነት በመጥቀስ።
የጉባኤው ተሳታፊ አቶ ወንድም በሪሁን እንዳሉት ብልጽግና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኀበራዊ ዘርፎች በርካታ ሥራዎችን አከናውኖ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በቀጣይም የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ይተጋል ብለዋል። ሌላዋ የጉባኤው ተሳታፊ አዲሴ አያሌው ፓርቲው ባሕር ዳር ከተማን ነጥለን ብንመለከት እንኳ ግዙፉ የዓባይ ድልድይ የተገነባው በብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪነት ነው ብለዋል።
“በተለይ ሴቶች የመሬት እና የሃብት ባለቤት እንዲኾኑም ፓርቲው ሠርቷል፤ ተጨባጭ ለውጥም ተመዝግቧል” ነው ያሉት። የመሬት እና ማዕድን መሠረታዊ ድርጅት መሬት፣ መስኖ እና ቆላማ አካባቢ፣ ማዕድን ሃብት ልማት፣ የውኃ እና ኢነርጂ ሃብት ቢሮዎችን እንዲሁም የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣንን ያቀፈ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!