የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

75

ባሕር ዳር: ጥር 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የአሥተዳደር መሠረታዊ ድርጅት የፓርቲውን ቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንስ ማካሄድ ጀምሯል። የመሠረታዊ ድርጅቱ ሰብሳቢ ግዛቸው ሙሉነህ ኮንፈረንሱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባኤ የሚደረገው ኮንፈረንስ አሳታፊነትን ለመጨመር እና በጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ እንደ አባል እና አመራር አስተዋጽኦ ለማድረግ መኾኑን ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች፦

👉 ከአንደኛው ጉባኤ ወዲህ የተሠሩ ሥራዎች እና አመራር እና አባላት ያሉበትን ደረጃ በመወያየት መገምገም፣
👉 የኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ሪፖርት፣
👉 በሚሻሻሉ የፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ክፍሎች ላይ ውይይት ማድረግ፣
👉 የአመራር እና አባላት ግምገማ እና ምዘና ማድረግ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለጉባኤ የሚሳተፉ አባላትንም ምርጫ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ እና መንገድ ኢትዮጵያ የምታደርገውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብት እና በዲፕሎማሲው መስክ የተመዘገቡ ድሎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ግዛቸው ያለፍንባቸውን የስኬት እና የፈተና መንገዶች እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ተገንዝበን በሚገባ ለማስረዳት እና የድርሻችን ለማበርከት ይህንን መድረክ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በቂ ተልዕኮ ለመውሰድም በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። እንደ አባል እና አመራርም ብቁ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል ትጥቅ መያዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እንደ ፓርቲ በጉባኤው የቀጣይ የሀገራችን መዳረሻም የሚመላከትበት እና አቋም የሚያዝበት፣ ወደ ተቀራረበ የአፈጻጸም ብቃት የምንመጣበት እና ወደ ሥራ የሚገባበት መኾኑን ጠቅሰዋል።

በሃሳብም ኾነ በተግባር ብልጽግናዎች ኾነን መንቀሳቀስ የሚያስችል አቅም የምንፈጥርበት መድረክ ይኾናል ነው ያሉት። ስኬቶችን በሚገባ ለይቶ ለነገው ተልዕኮ አዎንታዊ ሚና ለመጫዎት ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይቶ በመሠረታዊ ድርጅትም መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ ግዛቸው።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊ የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ፓርቲው ከአስቀመጠው አኳያ የተመዘገቡ ድሎችን እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በየደረጃው መዋቅሮች እየተገመገመ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም በየዘርፎቹ በርካታ ውጤቶች እና ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

የቆዩ እና የተዛቡ ትርክቶች የፈጠሯቸው ለውጡን ሊመልሱ የሚችሉ ግጭቶችን በማስወገድ ወንድማማችነትን፣ አሰባሳቢነትን ሊያመጡ የሚችሉ የብልጽግና ፕሮግራሞችን በገዥ ትርክትነት ለመገንባት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልላችንም ይህንን ኮንፈረንስ ስናስኬድ በችግር ውስጥ ኾነን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ለይተን ያጋጠመንን ችግር ማለፍ በምንችልበት ሁኔታ ላይም እንመክራለን ነው ያሉት።

ከኮንፈረንሱ አባላት ሀገራዊ አንድነትን፣ ብሔራዊነትን፣ አሰባሳቢነትን፣ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በሚያመጡ የኢትዮጵያን ብልጽግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ አቅጣጫዎችን ቆጥሮ ይዞ ለቀጣይ ራስን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ451 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠበሠበ።
Next article“ብልጽግና ፓርቲ በፈተናዎች ውስጥ ኾኖም ውጤቶችን አስመዝግቧል” አቶ ሲሳይ ዳምጤ