
ባሕር ዳር: ጥር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰልጣኝ የሚሊሻ እና የሰላም አሥከባሪ አባላትን አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኢትዮጵያ ታሪክ በጦርነት የተፈተነ መኾኑን አንስተዋል። የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች ተባብረው ሊወጓት፣ ዝቅ ሊያደርጓት እና ሊያፈርሷት ያልሞከሩበት ጊዜ የለም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በልጆቿ አንድነት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ናት ብለዋል። ጠላቶቻችን እንድንፈርስ፣ እንድንከፋፈል፣ ዝቅ ብለን እንድንታይ ይፈልጋሉ ነው ያሉት። የገጠሙንን ችግሮች ያለፍናቸው እንደ እናንተ ዓይነት ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል ለተመራቂዎቹ። የአማራ ክልልን ከአስከፊ የጸጥታ ችግር ያወጣው እና ከመፍረስ የታደገው የጸጥታ ኃይሉ መኾኑንም ተናግረዋል። ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችም ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ሰላም ከጊዜ ጊዜ እንዲመለስ የነበረውን ጥረት አድንቀዋል። ነውረኛ እና ቅጥረኛ የኾነው ኃይል ማፈር አለበት ነው ያሉት። ሰላሙ የተጠበቀ ከተማ እንዲኖር የጸጥታ ኃይሉ ወሳኝ መኾኑን ነው የተናገሩት። ቀውሱ በተፈጠረ ጊዜ በእምነታቸው ያልጸኑ እና በቃላቸው ያልረጉ ነበሩ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝብ እና መንግሥት የሰጣቸውን ኀላፊነት ትተው፣ ሕዝብ እና መንግሥትን ከድተው የራሳቸውን ወገን የወጉ አሉ ብለዋል።
እናንተ ታማኝ የሕዝብ ልጆች ናችሁ፤ በእምነታችሁ ጸንታችሁ የከተማችን ሰላም ስላስጠበቃችሁ፣ ታማኝ ልጆች ስለኾናችሁ አመሰግናችኋለሁ ነው ያሉት። “በክህደት ሀገርን እና ወገንን መውጋት ትርፉ ውርደት እንጂ ክብር ሊኾን አይችልም” ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማን ሰላም ለመንሳት ያልተደረገ ጥረት እንዳልነበረ ነው የተናገሩት። ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ኃይል የአማራ ልጆችን ይገድላል፣ አንድነቱን ይከፋፈላል፣ ክብሩን ይነካል፣ ልጆቹን በግፍ ይጨፈጭፋል ነው ያሉት። ሕዝብን የሚወጋውን ኃይል በተባበረ ክንዳችን ሕልሙን እያጨለምነው መጥተናል፣ ነገም እንዳይሳካለት አድርገን እስከወዳኛው መሸኘት አለብን ብለዋል። እናንተ እያላችሁ የባሕር ዳርን ሰላም ማወክ አይቻልም ነው ያሉት። እናንተ ታማኝ የሕዝብ ልጆች፣ ለታመናችሁበት ዓላማ ጸንታችሁ የቆማችሁ ናችሁ ብለዋቸዋል።
ሥልጠናው በስኬት መጠናቀቁንም ተናግረዋል። የሥልጠናው በስኬት መጠናቀቅ ለሰላም ፈላጊው ሕዝብ እና መንግሥት ትርጉሙ ትልቅ መኾኑንም ገልጸዋል። ድል አድራጊዎች እና አሸናፊዎች መኾናችን የምናሳይበት ነው ብለዋል። በቅንነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል። ሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ በሰላም ጊዜ ለልማት የሚሠማራ፣ ችግር በገጠመ ጊዜ ደግሞ ለሀገር እና ለሕዝብ ብሎ የሚሰለፍ መኾኑን ነው የተናገሩት። የከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላቸው ነው የገለጹት። ሥልጠናው እንዲሳካ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!