“ሀገር እና ሕዝብን የካደ ታሪክ የለውም” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

68

ባሕር ዳር: ጥር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ አባላትን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው የጸጥታ አካላት ሀገር እና ሕዝብ አደጋ ላይ ሲወድቁ ዋጋ እየከፈሉ ሀገር ያስቀጠሉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ዛሬ ላይ መሰባሰባችን እና አንድ ኾነን ለደስታ መብቃታችን ቀላል ደስታ ይመስላል ያሉት ኀላፊው ያለፍንበት ታሪክ እጅግ ውስብስብ እና አሰልች ነበር ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት የተገነቡ ያልተገሩ አስተሳሰቦች ሀገር እና ሕዝብ ዋጋ እያስከፈሉ መምጣታቸውንም ገልጸዋል። ያልተገሩ አስተሳሰቦች ማዶና ማዶ እንድንተያይ፣ ጠላትና ወዳጅ እንድንባባል፣ የታላቅ ታሪክ ባለቤቶች ኾነን ሳለ በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንድንቆይ አድርገውናል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ በአስቸጋሪ የጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት እና የክልሉ ሕዝብ በከፈሉት ዋጋ ሀገር የማጽናት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በሰሜኑ ጦርነት እና በልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት በነበሩ ሂደቶች የተፈጠሩ የጽንፈኝነት አመለካከቶች ጫፍ እየያዙ መጥተው ክልሉ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርገው መቆየታቸውን ነው የተናገሩት። የክልሉ የጸጥታ ችግር መታወክን ለመቋቋም እና ወደ ነበረት ለመመለስ መስዋእትነት እና ቁርጠኝነትን ይጠይቅ እንደነበር ነው ያስታወሱት። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እና አስተዋዩ ሕዝብ በሠሩት ሥራ ክልሉ ከጸጥታ ችግር እየወጣ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሰላም የሚረጋገጠው በሰላም እና በውይይት እንጂ በጦረኝነት እሳቤ አለመኾኑንም አስገንዝበዋል።

የሕዝብ ሰላም አምባሳደር ለመኾን የሥልጠና ሂደት አልፋችሁ ለምርቃት የበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት። ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው ያሉት ኃላፊው ያለ ሰላም የሚለማ ከተማ የለም፣ ያለ ሰላም ቱሪዝም፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ወጥቶ መግባት የለም ብለዋል። ሕዝብ ከጸጥታ ችግር የሚሻገረው በአንድነት እና በኅብረት መቆም ሲቻል መኾኑንም አመላክተዋል። ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በኀብረ ብሔራዊነት እና በኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል። ያለ አንድነት እና ወንድማማችነት የሀገር ሰላም ሊጸና አይችልም ነው ያሉት።
በሥልጠናው የተሰጡ ሥልጠናዎች ተጨማሪ አቅም ናቸው ያሉት ኀላፊው ትልቁ አቅም ግን አመለካከት ነው ብለዋል።

ብዙ ትጥቅ ለውጊያ ወሳኝ ቢኾንም ትልቁ ምሽግ ግን አመለካከት ነው ብለዋል። ለሕዝብ መስዋዕትነት ለመክፈል የወሰነ በደሙ ሀገርን ያጸናል ነው ያሉት። የአመለካከት አንድነት እና አስተሳሰብን መረዳት አስፈላጊ መኾኑን አሳስበዋል።
የአመለካከት ጥራት እና ወታደራዊ ሥነ ምግባር ያለው ኃይል ለመገንባት ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ባሕርዳር ከተማ ተናፋቂ እና ትልቅ ሃብት ያላት ናት ያሉት ኀላፊው ከተማዋን ልንከባከባት እና ዋጋ ልንከፍልላት ይገባል ነው ያሉት። ሕዝብ ዋጋ እየከፈለም ቢኾን ከመንግሥት ጎን ነው ብለዋል። ለሕዝብ መሞት ክብር መኾኑንም ተናግረዋል። ሀገር እና ሕዝብን የካደ ታሪክ የለውም ነው ያሉት። የቀደሙ አባቶቻችን ስም ዛሬ ላይ የምናነሰው ታሪክ ስላላቸው ነው ብለዋል። የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

ባሕርዳር ሰላም የሰፈነባት ከተማ እንድትኾን ተባብረን እንሠራለን ነው ያሉት። ሌብነትን እና አድሎን በመጸየፍ የአማራ ክልልን ሕዝብ ክብር ከፍ የሚያደርግ ሥራ እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የውኃ ኘሮጀክቶች ተመረቁ።
Next articleየሀገር ፍቅር ያለው ትውልድ መገንባት የብልጽግና ፓርቲ ዋና ዓላማ ነው።