በደቡብ ወሎ ዞን ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የውኃ ኘሮጀክቶች ተመረቁ።

38

ደሴ: ጥር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተሁለደሬ ወረዳ እና በሐይቅ ከተማ የተገነቡ የውኃ ፕሮጀክቶች የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በተገኙበት ተመርቀዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሠጡ የሐይቅ ከተማ እና የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በቂ ያልኾነ የውኃ አቅርቦት ያገኙ እንደነበር ገልጸዋል።

ለሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር መቀረፉ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል። የንጽሕ መጠጥ ውኃ ለማግኘት ብዙ እንገላታ ነበር፣ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ ጥያቄያችንን በመመለሱ ከብዙ ድካም አርፈናል ነው ብለዋል። በሐይቅ ከተማ የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾኖ የሚነሳው የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ነው ያሉት የሐይቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር መሐመድ ዛሬ የተመረቀው የውኃ ፕሮጀክት የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥያቄ መመለስ ይችላል ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ልማት ከሰላም ውጭ የማይታሠብ በመኾኑ የአካባቢያችሁን ሰላም አስጠብቃችሁ በመቆየታችሁ ጥያቄያችሁ ሊመለስ ችሏል ብለዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኅላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር ) የተገነቡት ሁለቱ የውኃ ተቋማት ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው እና ከ100 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።
ኅብረተሰቡ የውኃ ምንጮቹ እንዳይበከሉ እና እንዳይበላሹ መንከባከብ እና ከውኃ ተቋማቱ ጋር በትብብር መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል ቢሮ ኃላፊው።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታውን መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በገጠር እና በከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖር የክልሉ መንግሥት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።
የውኃ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ሠርቶ ለማስረከብ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ የተሠሩ ፕሮጀክቶችን ማኅበረሰቡ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የበኩሉን ኀላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተወያዩ።
Next article“ሀገር እና ሕዝብን የካደ ታሪክ የለውም” አቶ ደሳለኝ ጣሰው