
ገንዳ ውኃ: ጥር 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ከዞን፣ ከከተማ እና ከወረዳ አመራሮች ጋር ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤውን በገንዳ ውኃ ከተማ እያካሄደ ነው። የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እያሱ ይላቅ ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት በአንድ በኩል ችግሮችን ከመሠረቱ ነቅሎ ለመጣል በሌላው በኩል ደግሞ የቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስኑ አዳዲስ እሳቤዎችን በመያዝ ሕዝቡን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር የሚተጋ መኾኑን ተናግረዋል።
ገና በጨቅላ ዕድሜው ፓርቲው በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ችግሮችን እንዳመጣጣቸው በመመከት አኩሪ ድሎችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጣቸውን ዓላማ እና ግቦች ለመፈጸም ፓርቲው በየሁለት ዓመት ተኩል ጉባኤ ማካሄድ እንዳለበት ኀላፊው ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ፓርቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአመራሩ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ሊያመጡ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን እንዲረዱ የሚያስችል አጫጭር ሥልጠናዎችን ሲሠጥ ቆይቷል። አሥተዳዳሪ አክለውም እንደ ሀገር የገጠመውን የኢኮኖሚ ስብራት ለማከም እና ለማስተካከል ብልጽግና በችግርም ውስጥ ኾኖ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል። ፓርቲው ከነጠላ ትርክቶች ወጥቶ ወደ ጋራ የማንነት እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚገነባ ትርክት እየሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። ፓርቲው በችግር ውስጥ ኾኖ የተቋረጡ እና የተጀመሩ መሠረተ ልማቶችን መሥራቱ ይታወቃል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!