
ባሕር ዳር: ጥር 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በጠላት ወረራ ዘመን በዚህ ሳምንት ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም የተመሠረተ ድርጅት ነው፡።
አባላቱ በአምስት ዓመቱ የትግል ዘመን እነዚያ ወጣት ኢትዮጵያውያን አንጀታቸውን ለረሀብ፤ እግራቸውን ለሾህ እና ለጠጠር፤ ግንባራቸውን ለጥይት አጋልጠው ሀገራቸውን የጠበቁ ጀግኖች ናቸው፡፡
እነዚህ ጀግኖች ሞትም ቢመጣ እናት ሀገራቸውን አሳልፈው ለጠላት ላለመስጠት፤ ነፃነታቸውን ለጊዜያዊ ሹመት ብሎም ለሽልማት ላለመለወጥ ችግሮችን የተጋፈጡ ጀግኖች ናቸው።
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፤ ይህ ማኅበር በአርበኝነት ዘመን በሸዋ ክፍለ ሀገር በ1931 ዓ.ም «የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማኅበር» በሚል ስም ተሠይሞ የተቋቋመ ማኅበር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
ከመሥራች ማኅበረተኞች መካከልም ራስ አበበ አረጋይ፤ ወንድማማቾቹ ደጃዝማች ፀሐዩ እና ደጃዝማች ተስፋዬ ዕንቁ ሥላሴ፤ አቶ እምአእላፍ ኅሩይ፤ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፤ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋርያት ተጠቃሾች ናቸው።
በመጀመሪያ ጊዜ የነበሩት መሥራቾች ሃያ ዘጠኝ ሲኾኑ በኋላ ግን ብዙዎች ተቀላቅለው ከ300 በላይ መድረሳቸው ይነገራል።
✍️የንጉስ ተክለ ሃይማኖት እረፍት!
ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እና አድዋ ትልቅ ቁርኝት አላቸው፤ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ጦርን ይዘው ወደ አድዋ በመዝመት የድሉ አንድ አካል የነበሩ ጀግናም ናቸው፡፡
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጎጃም ገዥ ለመኾን ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ በቀድሞዋ መንቆረር በአሁኗ ደብረ ማርቆስ የሚገኘዉ የጎጃም ገዥዎች ቤተ መንግሥት በ1845 ዓ.ም ደጃዝማች ካሳ (ኋላ ዳግማዊ ቴዎድሮስ) የጎጃምን ግዛት ለማደላደል ዘመቻ አድርገው ክረምት በ1845 መንቆረር (አሁን ደብረ ማርቆስ) ውስጥ ቤተ መንግሥቱ በሚገኝበት ቦታ የሳር ሰቀላ ቤቶችን አሰርተው መክረማቸው እና በቦታውም ከተማ እንዲቆረቆር ትዕዛዝ ስለማስተላለፋቸው የቤተ መንግሥቱ ጅማሬም ለደጃዝማች ካሳ እና ለደጃዝማች ተሰማ ጎሹ (ለንጉስ ተክለ ሃይማኖት አባት) መካረሚያ ከተሠሩ ጎጆች እንደኾነ ይነገራል፡፡
እነዚህን የሰቀላ የሳር ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን እድሳት በማከናወን ደጃች ተድላ ጓሉ (1847-1860)፣ ደጃች ንጉሴ ተድላ(1860)፣ ደጃዝማች ደስታ ተድላ(1860-1861) እንደ ሁኔታው ጎጃምን ሲገዙ ቆይተውበታል፡፡
ከደጃዝማች ደስታ ተድላ በኋላ ጎጃምን የገዙት ራስ አዳል ተሰማ(ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) በዘመናቸው የቤተ መንግሥቱን የውስጥ አደረጃጀት በማስፋፋት የአሥተዳደር ሥራ በተደራጀ መንገድ እንዲከናወን በመደረጉ እና በሳር ክዳን ሰፊና ትልቅ አዳራሽ አሠርተው ስለነበር በአካባቢው ማኅበረሰብ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት በሚል ስያሜ መጠራት እንደጀመረ ይነገራል፡፡ ሥያሜው ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በኋላም ሳይለወጥ የአሁኑ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 263 ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሱዳን ደርቡሾች ድንበር ተሻግረው ጎንደር ድረስ በመግባት ጥር 10 ቀን 1880 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያን አቃጥለው ሰው ሲገሉ በወቅቱ አጼ ዮሐንስ አስመራ ስለነበሩ ይህንን በቀል ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እንዲበቀል መልዕክት በመላካቸው ንጉስ ተክለ ሃይማኖት 100 ሺህ የሚኾን ሠራዊታቸውን ይዘው በመሄድ ድል አድርገዋል፡፡
ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት በር በከፈተው ታላቁ የአድዋ ጦርነት ወቅትም የጎጃምን ጦር በመምራት 3 ሺህ ሠራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል፡፡
የግዛት ዘመናቸውም ራስ አዳል ተሰማ ተብለው ከ1861-1872 ዓ.ም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተብለው ከ1873-1893 ዓ.ም በአጠቃላይ ለ32 ዓመት ጎጃምን ማሥተዳደር ችለዋል፡፡
በዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ጎጃም ሲፈጽሙ ኑረው በዚህ ሳምንት ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም በእለተ አርብ ደብረ ወርቅ ላይ አርፈዋል፡፡
✍️የሊጎፍኔሽን ምሥረታ!
የያኔው ሊጎፍኔሽን የዛሬው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ተልዕኮው የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ የሚል ነው። የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ድርጅትም ነው።
ድርጅቱ የተመሠረተው ጥር 2 ቀን 1920 በፓሪስ ሲኾን የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ ሰላምን ለማምጣት ሲባል የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡
ሊጎፍኔሽን ወይንም በአሁኑ አጠራሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘመናዊው ዓለም አቀፋዊ አሥተዳደር አብነት እንደመኾኑ ዘመናዊውን ዓለም በጥልቅ ቀርጿልም ይባልለታል።
የድርጅቱ ዋና ግቦች በግልጽ ተቀርጾ እንዲቀመጥ የተደረገ ድርጅትም ነው። ጦርነቶችን በጋራ ደኅንነት እና ትጥቅ በማስፈታት መከላከል እና ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን በድርድር እና በግልግል መፍታትን መሠረት አድርጎም ብዙ እንደሠራ ይነገርለታል፡፡
ድርጅቱ የሰዎች እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ የጦር መሳሪያ ንግድ፣ የዓለም ጤና፣ የጦር እስረኞች እና በአውሮፓ ውስጥ ያሉ አናሳዎች ጥበቃን በተመለከተም የሚታይ ሥራ ሠርቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል ኪዳን ሰኔ 28 ቀን 1919 ስምምነት ክፍል አንድ የተፈረመ ሲኾን ከተቀረው የስምምነት ውል ጋር ጥር 10 ቀን 1920 ተፈፃሚ መኾን ችሏል።
የሊጎፍኔሽን ምክር ቤት የመጀመሪያ ሥብሠባ የተካሄደው ጥር 16 ቀን 1920 ሲኾን የመጀመሪያው የሊግ ጉባኤ የተካሄደው እ.ኤ.አ. ኅዳር 15 ቀን 1920 ነበር፡፡
ይህ ድርጅት በሚጠበቅበት ደረጃ በዓለም ላይ ባሉ ኀያላን ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና ጦርነቶች እንዲቆሙ ማድረግ ባይችልም የዓለም ሰላም እንዲረጋገጥ ግን ጥረት ማድረጉ ነው የሚገለጸው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation