
ሁመራ: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ ተጀምሯል። በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አሸተ ደምለው “ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ሀገራዊ ስብራቶች እንዳይደገሙ ለትውልድ መታመን አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ፓርቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ድሎች ብልጽግና ፓርቲ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ እንዳሳካቸውም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ፓርቲው ያሳካቸው ድሎች እና የፈጠራቸው እምርታዎች ከዕቅድ በላይ መኾናቸውን አስረድተዋል።
ፓርቲው ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ አዳዲስ አባላትን በማፍራት እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ኀላፊው አብራርተዋል።
ጉባኤው ነገም ቀጥሎ የሚካሔድ ሲሆን ባለፍት ሁለት ዓመት ተኩል የተገኙ መልካም ዕድሎች፣ በጎ ተግባራት እና አፈጻጸሞች፤ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!