ለኢትዮጵያውያን እና መንግሥታቸው ያልተደረገ ድጋፍ እንደተደረገ አድርጎ ማውጣት ተገቢ እንዳልኾነ የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተማላሾች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

48

ባሕር ዳር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት የመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስጠልላ ከለላ እና የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የምትገኝ ሀገር እንደኾነች የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተማላሾች አገልግሎት ገልጿል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በስደተኞች ስም የመጣ ማንኛውም ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኀላፊነት ያለበት በመኾኑ ከዋና መሥሪያ ቤት ጀምሮ የስደተኛ ማዕከላት ድረስ የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያብራራው፡፡

በዚህም መሠረት የራሺያ ፌደሬሽን የደቡብ ሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እና በጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ብሎም ጥገኝነት ጠያቂዎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም (ዋፋ) በኩል 1ሺህ 632 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን የስንዴ ድጋፍ አድርጓል ነው ያለው።

የስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ ከተለያዩ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚደረግ ድጋፍ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሲከናወን መቆየቱ እና የአሁኑ ድጋፍም የተደረገው ለተመሳሳይ ዓላማ እንደኾነ የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተማላሾች አገልግሎት ጠቁሟል፡፡ ይህም በሩሲያ ኤምባሲ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ይፋዊ መግለጫዎች በግልጽ ተሰጥቷል ነው ያለው።

ኾኖም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ድጋፉ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት” እንደተደረገ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኙ መገንዘቡንም ነው ያብራራው፡፡

በመኾኑም በተለያየ መነሻ የተሳሳተ ዘገባ ያስተላለፉ እና በማስተላለፍ ላይ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት እና አካላት ይህንን የእርምት መረጃ ግምት ውስጥ በማስገባት የተሳሳተ መረጃን እንዲያርሙም ጠይቋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዩጋንዳ ገቡ።
Next articleበዋድላ ወረዳ የሰብል ቃጠሎ መድረሱ ተገለጸ፡፡