የኮምቦልቻ የአስፋልት ማሳለጫ መንገድ በዚህ ዓመት መጠናቀቅ እንደሚገባው የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) አሳሰቡ።

64

ደሴ: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የማሳለጫ መንገድ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል። በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የኮምቦልቻ መንገድ ኔትወርክ እና ደኅንነት ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር ቶፊቅ ሱለይማን መንገዱ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 23 ሜትር ስፋት እንዳለው ተናግረዋል።

የአራት ድልድዮች ግንባታ እና የውኃ ማፋሰሻ ግንባታ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ የተናገሩት ኢንጅነር ቶፊቅ ሱለይማን አጠቃላይ የግንባታው አፈፃፀም 22 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የተሰጣቸውን አስተያየት በመውሰድ በተለይ የግንባታ ዕቃዎች ቁጥር በመጨመር ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የመንገዱ ግንባታ የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያቃልል እና ለከተማዋ መስፋፋት እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት መኾኑን ነው የገለጹት። ለመንገዱ ግንባታ መጓተት ምክንያት ከኾኑት መካከል ከሦስተኛ ወገን ነጻ የማድረግ ውስንነቶች አንዱ ሲኾን ችግሩን ከተማ አሥተዳደሩ በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚሰጥም ከንቲባው ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት በካሳ ክፍያ ላይ ድጋፍ እንዲያደረግም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 61 የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸው ከነዚህ ውስጥ 27 የሚኾኑት በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በሥራ ተቋራጩ የተነሱት የጠጠር እና ግንባታ ግብዓት እጥረቶችን ለመፍታት ከደቡብ ወሎ ዞን ጋር በመተባበር እንዲቀረፍ ይሠራልም ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የኮምቦልቻ ማሳለጫ መንገድ በዚህ ዓመት መጠናቀቅ እንዳለበት አቅጣጫ ሰጥተዋል። ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ በተለይ “በከተማ አሥተዳደሩ በኩል የወሰን ማስከበር ቀሪ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ፣ በተቋራጩ በኩል ደግሞ ተጨማሪ የግንባታ እና የሰው ኀይል በመጨመር ግንባታውን ቀን ከሌት መሥራት ይገባል” ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ:- ከድር አሊ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በካሊፎርኒያ በደረሰው ሰደድ እሳት እና በተፈጠረው ጉዳት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ገለጸች።
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዩጋንዳ ገቡ።