የደሴ ከተማ አሥተዳደር ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የመፈጸም አቅም ማደጉን በተግባር አሳይቷል።

19

ደሴ: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል የደሴ ከተማ አሥተዳደር የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮች የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ ተጀምሯል። በጉባኤው በፓርቲው የእስካሁን ጉዞ ያጋጠሙ የአስተሳሰብ ዝንፈቶችን፣ የተከሰቱ ችግሮች እና የተገኙ ውጤቶች እየተገመገሙ ነው።

በደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ”በጫና ውስጥም ኾነን ሀገር በቀል በኾነ የመደመር እሳቤ ከራሳችን አልፈን ለጎረቤት ሀገራት ምሳሌ መኾን የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውነናል” ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን በማፅናት የብልፅግና ፓርቲ በፖለቲካው እና በኢኮኖሚው እንዲሁም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው።

በተለይ ፓርቲው ልዩነትን በሰከነ መልኩ በውይይት ለመፍታት የሄደባቸው መንገዶች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል። በመሠረተ ልማት ዘርፍ ታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተሠርተው መጠናቀቃቸው ፓርቲው ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመፈፀም አቅሙን ያሳየበት መኾኑም ተመላክቷል።

በባለፈው የበጀት ዓመት በደሴ ከተማ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውም በማሳያነት ተነስቷል። በአማራ ክልል ያሉ መዋቅራዊ፣ አሥተዳደራዊ እና የወሰን ጥያቄዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ መልስ እንዲያገኙ እየተሠራ ያለው በብልፅግና ፓርቲ የለውጥ እሳቤ መኾኑን በጉባኤው ተገልጿል።

ጉባኤው ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲኾን ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል።

ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተካሄዱ የለውጥ ሥራዎች ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next article“ብልጽግና ፓርቲ የገባቸውን ቃሎች በመፈጸም ሀገራዊ እና ገዥ ትርክቶችን ማጽናት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው” የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር