በተካሄዱ የለውጥ ሥራዎች ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

23

ባሕር ዳር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ”ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት ለሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ቅድመ ኮንፈረንስ ማድረግ ጀምሯል። በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሏቸውን በርካታ ጥያቄዎች የሚመልስ ለውጥ በመፈለጋቸው ለውጡ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት ፓርቲ መመሥረቱን እና በፓርቲው የመሪ ለውጦች መታየታቸውን ብሎም የሕዝቦች ተጠቃሚነት መኖሩን አንስተዋል። በኮንፈረንሱ በባለፈው የፓርቲው ጉባኤ የታቀዱ ሥራዎች ላይ የተሠሩ እና የቀሩት የሚገመገሙበት እንደሚኾንም ተናግረዋል። የቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ሥራዎች አቅጣጫ የሚቀመጥበት ይኾናልም ነው ያሉት።

ባለፉት የትግበራ ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች የሚታዩበት እና የከተማ አሥተዳደሩ ሥራዎች ጥንካሬ እና ድክመቶችም እንደሚገመገሙበት ገልጸዋል። የአመራር ችግሮችን በመፍታት ራዕይን ማሳካት፣ በኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር እንዲሁም በተሻሻሉ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች ላይ ውይይት እንደሚደረግም አቶ ሞላ ጠቁመዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ጽጌረዳ አበበ በኮንፈረንሱ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ብልጽግና ፓርቲ የነበረውን ስኬት እና ተግዳሮት በመገምገም የሠራቸውን ሥራዎች እና ለውጦች በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ነው የተናገሩት፡፡ አመራሩም ጠርቶ በመውጣት ብልጽግናን እንደሚያስቀጥል እና ለዚህም በአገልጋይነት ስሜት በመሥራት ሁሉም ካለበት ችግር በመውጣት የባከነውን ጊዜ ለመካስ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሌላኛው የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ዮናስ አሰፋ በኮንፈረንሱ የውስጥ ችግሮችን በመቅረፍ እና በትይዩም ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ወሳኝ መድረክ መኾኑን ገልጸዋል። ኮንፈረንሱ በየደረጃው ያለውን መሪ በማስተካከል የማኅበረሰቡን የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ችግሮች ለመፍታት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫዎታል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም ማስፈን ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን የምንከውነው ተግባር ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
Next articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የመፈጸም አቅም ማደጉን በተግባር አሳይቷል።