
ጎንደር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ተውጣጥተው ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ የሚሊሻ አባላት ተመርቀዋል። በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም ችግር ለመፍታት ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄድ እና የጸጥታ አካላትን የማሠልጠን ተግባር ሲከወን ቆይቷል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለጸጥታ መዋቅሩ አጋዥ ለኾኑት የዕለቱ ተመራቂዎች አካባቢያቸውን ሰላም ለማድረግ ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ጎንደር እና አካባቢው ሰላም እንዲኾን መደራጀት እና አንድነት መፍጠር ቀዳሚው ጉዳይ መኾን አለበት ብለዋል። “ሰላም ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን የምንከውነው ተግባር መኾን ይገባዋልም” ነው ያሉት።
አሰግድ ስማቸው እና ዳኛው ካሤ ሥልጠናውን በተገቢው መንገድ ወስደው መመረቃቸውን ተናግረዋል። በሥልጠናው ባገኙት ልምድ አካባቢያቸውን ሰላም ከማድረግ ባለፈ ጥያቄ አለን ብለው ወደ ጫካ የገቡ ወንድሞቻቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራም እንሠራለን ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ወስደው ወደ ተግባር የገቡ የሚሊሻ አባላት በከተማዋ ሰላም እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገለጹት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አግየ ታደሰ ከተማው ሰላም ሰፍኖበት ወደ ሙሉ ልማት እንዲመለስ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
አካባቢውን ሰላም ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ማኅበረሰቡ አጋዥ ሊሆን እንደሚገባም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!