
ባሕር ዳር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ”ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት የሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የቅድሚያ ኮንፈረንስ ማድረግ ጀምሯል። ኮንፈረንሱ የፓርቲው ጉዞ ምን እንደሚመስል፣ ችግሮች እና ውጤቶች የሚገመገሙበት እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጥበት መድረክ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በብልጽግና ፓርቲ የተመራው ለውጥ በኢትዮጵያ ካሳየው ውጤት ትምህርት መውሰድ እንዲቻል ጉባኤው አስፈላጊ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ በእስካሁኑ ጉዞ በችግርም ውስጥ ተኹኖ ሀገርን ከመፍረስ አደጋ ማዳን መቻሉን ነው አቶ ጎሹ ያነሱት።
በአፍሪካ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያስቻለ አመራር ስለመኖሩ የተረጋገጠበት ነው ብለዋል። በጉባኤው እስካሁን የተመጣበትን የአመራር ጥበብ በመመርመር ዘመን ተሻጋሪ ውሳኔ የሚቀመጥበት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በሂደቱ በአመራር ምን ጉድለት እና ጥንካሬ እንደነበረ እንደሚታይ አስረድተዋል። ሰላምን ለማስፈን እና ልማት ለማምጣት የነበረውን ጥንካሬ እና ቅንጅት ብሎም ድክመቶች እንዳይደገሙ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ ድክመት እና ጥንካሬዎች ታይተው ለቀጣይ አመራር ግብዓት የሚገኝበት መኾኑን ገልጸዋል። ራዕይ እና ጥራት ያለው አመራር ለመፍጠርም ኮንፈረንሱ ይሠራል ብለዋል። የመሪዎች ግምገማ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት። በማጥራት እና በማስተካከል ጠንካራ መሪ የሚፈጠርበትም እንደሚኾን ገልጸዋል።
ልማትን ለማረጋገጥ የሚሠራውን እና የሂደቱን ችግሮች መፍቻ መፍትሄ አስቀምጠው እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!