በላሊበላ ሴት አስጎብኝዎች እንዲበራከቱ እየተሠራ ነው።

26

ወልድያ፡ ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች አስጎብኝዎች በብዛት ወንዶች ናቸው። በቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢ አስጎብኝ ማኅበር ውስጥ አሁን ላይ 165 አስጎብኝዎች ያሉ ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሴት ብቻ ትገኛለች። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ደግሞ ሴት አስጎብኝዎች እንዲበራከቱ ይፈልጋል። ጎብኝዎችም ለጉብኝት ሲመጡ ሴት አስጎብኝዎች ለምን እንደማይኖሩ ይጠይቃሉ ነው የተባለው። አሁን ላይ በከተማ አሥተዳደሩ ሴት አስጎብኝዎችን ለማበራከት እየተሠራ ነው። በአስጎብኝነት ሙያ የተሰጠው ሥልጠና ሴቶችን አሳታፊ እንደሚያደርግ እና ለምን በአስጎብኝነት አይሳተፉም የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው ተብሏል።

ካዌ የተባለው ድርጅት ደግሞ ሴቶችን በማደራጀት በአስጎብኝነት ሙያ ተሳታፊ እንዲኾኑ ሥልጠና መስጠቱ ነው የተገለጸው። ድርጅቱ ለ20 ሴቶች በአስጎብኝነት ሙያ ሥልጠና መሥጠቱም ተመላክቷል። በካዌ ድርጅት የቪዚት ላሊበላ ፕሮጄክት አማካሪ ኃይሌ ንጋቴ ካዌ ቪዚት ላሊበላ ብሎ በአራት የሙያ ዘርፎች ለሴቶች ሥልጠና እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል። የአስጎብኝነት ሙያ ደግሞ አንዱ የሙያ ዘርፍ መኾኑን ነው የተናገሩት። ድርጅቱ 20 ሴቶችን አሠልጥኖ በዘርፉ እንዲሠማሩ ሂደት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። በዘርፉ ለሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ሴቶችም በአስጎብኝነት ሙያ መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ መኾኑንም አመላክተዋል። በካዌ ድርጅት የአስጎብኝነት ሥልጠና የወሰደችው አጸደ አበበ በአስጎብኝነት ሙያ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ መኾኑን ገልጻለች። ሴቶች በብዛት በማይሳተፉበት የሙያ ዘርፍ ለመሳተፍ ሕልም ሰንቃ እየሠለጠነች መኾኗን ነው የተናገረችው።

በኮሎጅ ደረጃ ለአራት ዓመታት መማራቸውንም ገልጻለች። በካዌ ድርጅት ደግሞ የእንግዳ አቀባበል እና ሌሎች ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን ነው የተናገረችው። ሥልጠናውን ጨርሰው የመጨረሻውን ፈተና እና ፈቃድ እየጠበቁ መኾናቸውን ገልጻለች።

የተሻለ አስጎብኝ ለመኾን በሥነ ልቦና እና በትምህርት ዝግጁ መኾኗንም ተናግራለች። የአካባቢው ባሕል፣ ሃይማኖት እና ታሪክ ላይም የተሻለ ግንዛቤ እንዳላት ነው የተናገረችው። ካዌ ሴቶች ብቁ እንዲኾኑ ለማድረግ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚመሠገን ነው ብላለች። በአስጎብኝነት ሙያ በመሳተፍ ለቅርሱ ጸጋ የመካፈል ሕልም እንዳላትም ተናግራለች።

ሌላኛዋ ሠልጣኝ ወርቅአፈራሁ ቅባቱ የካዌ ድርጅት ከኮሌጅ ተመርቀው ሥራ አጥ በኾኑበት ጊዜ ሥልጠና እንደሰጣቸው ገልጻለች። ሥልጠናው ሴቶችን የሚያበረታታ እና ሴቶች በብዛት በሌሉበት ሙያ በአስጎብኝነት ሙያ የሚያሳትፍ ነው ብላለች።

ካዌ ድርጅት ተግባራዊ ልምምድ እንደሰጣቸውም ገልጻለች። በቂ ክህሎት መያዛቸውንም ተናግራለች። ወደ ሥራው ለመግባት የመጨረሻውን ፈተና እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጻለች። ለማስጎብኘት የሚጠበቅባቸውን ክህሎት ማግኘታቸውንም ተናግራለች። ሥልጠናው ሴቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የሚያደርግ ነው ብላለች።

ህልማቸው በሴት አስጎብኝዎች ያለውን እጥረት መፍታት እና ለጎብኝዎች በቂ አገልግሎት መሥጠት መኾኑንም ገልጻለች።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ተግባብቶ በመሥራቱ በከተማዋ በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት ተሠርተዋል” የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር
Next articleየመሪዎችን ዓቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።