የሀገር በቀል ስጦታዎች ምርት በላሊበላ!

24

ወልድያ: ጥር 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ላሊበላ የጎብኝዎች መዳረሻ ናት። ጎብኝዎች የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ለመጎብኘት ይጓጓሉ። በቆይታቸውም የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን የሚያስታውሱበት እቃዎችን መግዛት ይፈልጋሉ። ጎብኝዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚገለጥባቸውን የማስታወሻ እቃዎችን ይፈልጋሉ።

በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር አዲስ ጅማሮ ታይቷል። በማኅበር የተደራጁ ሴቶች በሀገር በቀል ዕውቀት እና የአካባቢውን ጥሬ እቃ በመጠቀም የስጦታ እቃዎችን እያመረቱ ለጎብኝዎች ማቅረብ ጀምረዋል። ይህ ደግሞ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የአካባቢውን ባሕል እና ማንነት በማስተዋወቅ፣ የጎብኝዎችን ፍሰት በመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

ሴቶችን ያደራጃቸው ካዌ የተሰኘው ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለሴቶች ሥልጠና በመስጠት ነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደረገው። ተጨማሪ ሥልጠናዎችንም እየሰጣቸው ነው። ሴቶቹ የተደራጁት በባሕላዊ ልብስ ሽመና፣ በማር ተረፈ ምርት፣ የሥጦታ እቃዎችን በመሥራት፣ በሸክላ የስጦታ እቃዎችን መሥራት እና በሴት አስጎብኝነት ነው።

በባሕላዊ ልብስ ሽመና የተሰማራችው ጉዝጉዝ ካሳው ካዌ የተሰኘው ድርጅት የሙያ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዳስገባቸው ተናግራለች። ተጨማሪ ሥልጠናዎችን እየሰጣቸው መኾናቸውንም ገልጻለች። ሥራው የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን ዘመናዊ ማሽኖችን መጠቀም ይገባል ብላለች። ማሽኖች ዘመናዊ ከኾኑ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ነው የተናገረችው።

ለጎብኝዎች ብቻ ሳይኾን ለአካባቢው ማኅበረሰብም የሚኾኑ ባሕላዊ አልባሳትን እንደሚያመርቱ ነው የገለጸችው። የማር ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የስጦታ ዕቃዎችን በመሥራት ከተደራጁት መካከል የዝና ይርዳው በማር ተረፈ ምርት ሻማ፣ የከንፈር ቅባት፣ ሳሙና እና ሌሎችን እንደሚሠሩ ነው የተናገረችው። ምርታቸው ተፈጥሯዊ መኾኑንም ገልጻለች።

የስጦታ እቃዎቹ ለጎብኝዎች ምቹ መኾናቸውንም ተናግራለች። ማር ከላሊበላ የስም ትርጓሜ ጋር እንደሚገናኝ የተናገረችው የዝና የማር ተረፈ ምርትን በመጠቀም ሀገር በቀል ዕቃዎችን ለጎብኝዎች እያቀረቡ መኾናቸውን ገልጻለች። የሥራቸው መለያም ላሊበላ እንደሚልም ተናግራለች ።

ጎብኝዎች እስካሁን የአካባቢውን ምርት ያገኙ እንዳልነበረ ነው የገለጸችው። ጎብኝዎች አካባቢውን የሚያስታውሱበት ምርት ማቅረብ የቱሪዝም ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል ነው ያለችው። ሥራው የተሻለ ቦታ እንደሚያደርሳቸውም ያላትን ተስፋ ገልጻለች።

ከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቃለች። በሸክላ የስጦታ እቃዎችን በማምረት ከተሰማሩት መካከል መሠረት ሲሳይ ባሕላዊ የሸክላ ሥራዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግራለች። ቤተ ጊዮርጊስን፣ ጎጆዎችን፣ አዕዋፋትን እና ሌሎች ቅርጻ ቅርጾችን በሸክላ ላይ እየሠሩ ለጎብኝዎች እንደሚያቀርቡ ነው የገለጸችው።

ለጎብኝዎች ብቻ ሳይኾን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለማቅረብ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግራለች። ሴቶች ብቻ በማኅበር ታቅፈው እንዲሠሩ መደረጉ እድለኛነት መኾኑን ገልጻለች። በካዌ ድርጅት የቪዚት ላሊበላ ፕሮጄክት አማካሪ ኃይሌ ንጋቴ ካዌ ቪዚት ላሊበላ ብሎ በአራት የሙያ ዘርፎች ለሴቶች ሥልጠና መስጠቱን ገልጸዋል። ተጨማሪ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መኾኑንም አመላክተዋል።

በሸማ ሥራ 15፣ በሸክላ ሥራ 15፣ በማር ተረፈ ምርት 50 ሴቶችን እና በሴት አስጎብኝዎች 20 ሴቶችን በድምሩ ለ100 ሴቶች ሥልጠና እየሠጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት ። ምንም አይነት የሥራ አማራጭ ያልነበራቸው ሴቶች በሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ተመልምለው መምጣታቸውን ገልጸዋል። ድርጅቱ ሥልጠና ሲሰጥ ግብዓት ገዝቶ መኾኑንም ተናግረዋል።

ሠልጣኞች ችግሮችን ተቋቁመው ውጤታማ እንዲኾኑ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ካዌ ለሚሠሩት ሥራ የገበያ ትስስር እየፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል። ለጎብኝዎች የስጦታ እቃዎች ያቀርቡ የነበሩት ከላሊበላ አካባቢ ውጭ ያሉ እንደነበሩ የተናገሩት አማካሪው ቪዚት ላሊበላ ብለው ሥራ ሲጀምሩ የአካባቢውን ምርት አምርቶ ለጎብኝዎች ለማቅረብ ዓላማ አድርገው መኾናቸውን ነው የገለጹት።

አካባቢውን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። ካዌ ሴቶችን ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ አንስቶ ለከፍተኛ የኑሮ ደረጃ የማድረስ ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ፍሬስብሐት ጌታቸው በኮሌጆች አማካኝነት ሥልጠና መስጠት፣ የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታ ማመቻቸት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የማምረቻ ሸዶችን መስጠታቸውንም ገልጸዋል። የመሸጫ ቦታዎችን ለመሥጠት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የገንዘብ ችግር እንዳይገጥማቸው ለመደገፍም እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ካዌ የተሰኘው ድርጅት የሥራ እና ሥልጠና ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ሥራ በመፍጠር እያገዛቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋድላ የደረሰው ጉዳት ከጉዳትም በላይ ነው።
Next article“መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ተግባብቶ በመሥራቱ በከተማዋ በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት ተሠርተዋል” የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር