በዋድላ የደረሰው ጉዳት ከጉዳትም በላይ ነው።

72

ባሕር ዳር: ጥር 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ ወረዳ በ11 ቀበሌዎች የሰብል ክምር ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ደርሷል፡፡ በዋድላ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ምክንያቱ ባልታወቀ የእሳት ቃጠሎ የ154 አርሶ አደሮች የሰብል ክምር መቃጠሉ ነው የተገለጸው፡፡

ጥር 1/2017 ዓ.ም በደረሰው ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደር ሲሳይ ፈቃዴ እና ሌሎቹም የቃጠሎው ተጎጅ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቃጠሎው መነሻ በውል አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ ተጎጅዎቹ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው አርሶ አደሮች መካከል የአንዳንዶቹ ከተቃጠለው ሰብል ውጭ ሌላ ምንም አዝመራ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ የዋድላ ወረዳ የአደጋ መከላከል እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ ምትኩ ሞላ በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች የእሳት ቃጠሎ መከሰቱን ገልጸው እስካሁን ባለው መረጃ 770 የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጉዳቱ ሰለባ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዋድላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉየ ረታ በወረዳው በ11 ቀበለሌዎች በ152 ክምር ላይ ቃጠሎ እንደደረሰ ነው ያስረዱት፡፡ በቃጠሎው 154 አርሶ አደሮች የጉዳቱ ሰለባ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል፡፡

ኀላፊው በደረሰው ቃጠሎ 4 ሺህ 560 ኩንታል የሚኾን የእህል ክምር ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረው ይህም ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቁመዋል፡፡

የጉዳቱ ሰለባ የኾኑ አርሶ አደሮችን ሁሉም እንዲያግዝ ወረዳው ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleድሎችን በማስፋት እና ስህተቶችን በማረም ሀገራዊ ለውጡ እንዲቀጥል እየተሠራ ነው።
Next articleየሀገር በቀል ስጦታዎች ምርት በላሊበላ!