
ወልድያ: ጥር 2/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት የጥገና ሥራ እየተሠራ መኾኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ጥገናው ምን ምን ያካተተ ነው? መቼ ተጀምሮስ መቼ ይጠናቀቃል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት የውጭ ግንኙነት ክፍል ኀላፊ እና የትኬት እና ሙዚየም ቢሮ ሥራ አሥኪያጅ ዲያቆን መኮንን ገብረመስቀል የላሊበላ ሕዝብ አብያተክርስቲያናቱ ጥገና እንዲደረግላቸው በሰልፍ ከጠየቀ በኋላ የተጀመረ መኾኑን ገልጸዋል።
በአብያተክርስቲያናቱ ላይ ያለው መጠለያ እንዲነሳ መጠየቁን አስታውሰዋል። መጠለያው ካልተነሳ በአብያተክርስቲያናቱ ላይ ችግር ያመጣል የሚል ስጋት በማኅበረሰቡ ዘንድ መኖሩን ነው የተናገሩት። በነፋስ ግፊት ምክንያት መጠለያው በአብያተክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር ያስታወሱት ዲያቆን መኮንን የመጠለያው የአገልግሎት ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ እንዲነሳ እና እንዲቀየር መጠየቁን ነው የተናገሩት።
መንግሥት ሕዝብ የጠየቀውን ጥያቄ በማዳመጥ ከፈረንሳይ መንግሥታት ጋር የቅርስ አድን ትብብር ፕሮጄክት ፊርማ መፈራረሙንም አስታውሰዋል። ስምምነቱ ከተፈጸመ በኋላ ጥናቱ ሦስት ዓመታት መውሰዱንም ተናግረዋል። ጥገና ለማካሄድ ዘጠኝ ጥናቶችን ማጥናት እንዳስፈለገ የተናገሩት ዲያቆን መኮንን ሰባቱ ጥናቶች ተጠንተው ሁለቱ ሳይጠኑ መቅረታቸውን ነው የገለጹት።
በዚህ መካከል በጣም አስቸኳይ የሚባሉ የቅርስ ልማት ሥራዎች እንዲሠሩ መደረጋቸውን ነው የተናገሩት። ዋናው እና መጠለያ ይነሳ ብሎ ሕዝቡ የጠየቀው ሥራ ግን አልተሠራም ነው ያሉት። የመጠለያ ማንሳት እና ሁሉን አቀፍ ፕሮጄክት ግን አልተጀመረም ብለዋል። በገዳሙ የተሠሩ ሥራዎች ጥናቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ድልድዮች፣ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ቋጥኞች፣ የአርኪኦሎጂ ሥራዎች፣ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት።
ዋናውን ሥራ ለመሥራት ሁለቱ ጥናቶች መጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል። ጥገና የተደረገላቸው ትንንሾቹ እና እንደመዳረሻ ልማት የሚቆጠሩት ናቸው ነው ያሉት። ትልቁ ፕሮጀክት ትልቅ አቅም እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። የቀሩትን ጥናቶች የሚያጠና ተቋም መቀጠሩንም ተናግረዋል። ፍላጎታቸውም ጥናቶቹ በፍጥነት ተጠናቅቀው ሥራው በፍጥነት እንዲጀመር መኾኑንም ገልጸዋል። መጠለያዎች ጊዜያቸው በረዘመ ቁጥር በአብያተክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ነው የተናገሩት።
ድንቅ የኾኑ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በፍጥነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት አሥተባባሪ ማንደፍሮ ታደሰ የላሊበላ ሕዝብ ቅርሱ እንዲጠገን በመጠየቁ መንግሥት ቅርሶችን ለመጠገን ፈጣን ምላሽ መስጠቱን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር መጥተው የቅርሱን ኹኔታ ማየታቸውን እና ከምልከታቸው በኋላ ደግሞ አጥኝ ቡድን መምጣቱን ነው የተናገሩት። የሕዝቡ ጥያቄ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ዘላቂ የኾነ ጥገና ያስፈልጋቸዋል የሚል ነው ያሉት አሥተባባሪው ዘላቂ ጥገናው ቀርሶቹ ላይ ያሉ ስንጥቆችን መጠገን፣ መጠለያውን ማንሳት እና በአዲስ እንዲተካ ማድረግ መኾኑን ነው የገለጹት።
ከዋናው ፕሮጄክት ቀድሞ ሌሎች የጥገና ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት ። በፕሮጀክቱ ቅዱስ ላሊበላ ሥርቷቸው ነገር ግን ተዳፍነው የቆዩ ሥራዎችን መመለስ፣ የአርኪኦሎጂ ቁፋሮ፣ የመዳረሻ ልማት፣ ድልድዮችን እና ሌሎችም መሠራታቸውን ገልጸዋል። በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖችም ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ነው የተናገሩት። እየተሠራ ያለው ሥራ ከዋናው እና ከትልቁ ፕሮጀክት የተለየ መኾኑንም ገልጸዋል።
ትልቁ ፕሮጀክት አለመጀመሩንም ተናግረዋል። ቅርሶቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ዋናውን ፕሮጄክት መጀመር ይገባል ነው ያሉት። ከዋናው ፕሮጄክት ቀድመው የተሠሩ ሥራዎች መልካም መኾናቸውንም ተናግረዋል። ጥራታቸው የተጠበቀ፣ ከቅርሱ ጋር የሚሄዱ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ምቹ የሚያደርጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ሰምቶ የጀመራቸው ሥራዎች ምሥጋና የሚያሰጡት ነው ያሉት አሥተባባሪው ጥናቶች በፍጥነት ተጠናቅቀው ዋናው ሥራ እንዲጀመር ማድረግ አለበት ነው ያሉት። የቅርሱ ዋና ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ከመንግሥት ጋር በመተባበር ጥናቱ እንዲጠናቀቅ እና ቅርሶቹ እንዲጠገኑ ማድረግ አለባት ብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በአግባቡ ተጠብቀው ለልጅ ልጅ እንዲተላለፉ ለማድረግ መንግሥት ወዳጅ ሀገራትን እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የቅርስ ጥበቃ እና ልማት ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።
በላሊበላ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ ሁለተኛ ዙር ሥራዎችን ለመሥራት ስምምነት ተፈርሞ በሂደት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!