
ባሕር ዳር : ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሦሥት ወረዳዎች የርዕደ-መሬት ክስተትን በተመለከተ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደናል፡፡ በአስቸኳይ ስብሰባችን የሳይንስ ማኅበረሰቡ አካላት እና የሁለቱ ክልሎች አመራሮችም እንዲሳተፉ አድርገናል።
ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል በኾኑ አካባቢዎች የተከሰቱ የርዕደ-መሬትና እና ንዝረት ስጋቶች በልዩ ትኩረት መከታተል የሚገባን መኾኑን ተግባብተናል፡፡
የክስተቱ ድግግሞሽ እና ስፋት በአካባቢው በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን በጋራ ግብረ ኃይል የተሠሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸውን ገምግመናል፡፡
የፌዴራል እና የክልል መዋቅሮች የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ምላሽ እየሰጡ መኾኑን እና የሳይንስ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለ መረጃ እየሰጠ መኾኑን አይተናል።
በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል አጋር አካላት እና የሚመለከታቸው ሴክተሮች የቅድመ መከላከል ሥራውን በትኩረት ደግፈዋል፡፡
በአስቸኳይ ስብሰባችን የርዕደ- መሬት ክስተቶች እና የተሰጡ ምላሾችን በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች እና ተግባራት ላይ አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡
እስካሁን በቅድመ መከላከል ውጤታማ ሥራው ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!