“ተገልጋዮች ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

9

ደሴ: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ስር የሚገኙ ተቋማት በተለያዩ አካባቢዎች ለተገልጋዮች አገልግሎትን ሲሰጡ ቆይተዋል። አንዳንድ መምሪያዎች ደግሞ የራሳቸው ቢሮ ስለሌላቸው ተከራይተው አገልግሎት ለመስጠት ተገደውም ነበር።

በዚህም ምክንያት አገልግሎት የሚፈልጉ ተቋማት እና ግለሰቦች ተገቢውን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በኪራይ ቤት ከነበሩ ተቋማት መካከል የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ልማት መምሪያ አንዱ ነው። የመምሪያው ኀላፊ አሕመድ አበባው ባለፉት ዓመታት መምሪያው ለኪራይ ብቻ በሚሊዮን ብር ለማውጣት ሲገደድ መቆየቱን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ የመንግሥት ንብረትም ደኅንነቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ደቡብ ወሎ ዞን ባስገነባው ሕንጻ ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንድሪስ ይማም በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ሥራዎች እየተመረቁ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ኀላፊው ዛሬ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት እና 21 የዞኑን ተቋማት የሚይዘው ግዙፉ ሕንጻ ከተመረቁት ውስጥ አንዱ እንደኾነ ጠቁመዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “የሠራተኞችን የሥራ ተነሳሽነት ለመጨመር እና ተገልጋዮች ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ደረጃቸውን የጠበቁ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

በቀጣይ የሚጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እና የተቋማት ግንባታን በተያዘላቸው ጊዜ እና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደሴ ሙዚየም 90 በመቶ የጥገና ሥራው መጠናቀቁ ተገለጸ።
Next article“የሥራ ኀላፊዎች ራሳቸውን ለመፈተሽ እና ብልሹ አሠራሮችን ለማረም ዝግጁ መኾን አለባቸው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር