የደሴ ሙዚየም 90 በመቶ የጥገና ሥራው መጠናቀቁ ተገለጸ።

17

ደሴ: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ጉዳት እና ዘረፋ ደርሶበት የነበረው እና የታሪክ ማኅደር የኾነው የደሴ ሙዚየም ከቀድሞ ይዞታው በተሻለ መንገድ መልሶ የማደስ ሥራ ሢሠራ ቆይቷል። ጥገና በተደረገበት ሙዚየም ውስጥ የሚቀመጡ ቀሪ የሙዚየሙ ሃብቶችን ማሠባሠብ ያለመ እና የጠፉ ቅርሶችን ማስመለስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ ሙዚየሙ ነባር ይዘቱን እንዳይለቅ አድርጎ ከመጠገን ባለፈ ሌሎች ዘመናዊ ሙዚየሞችን ካሉበት ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ የተለያዩ ዕሴቶችን በመጨመር ታሪካዊነቱን ጠብቆ መታደሱን ገልጸዋል። በዚህም 90 በመቶ የሚኾነው የጥገና ሥራ መጠናቀቁን ጠቅሰው የእድሳቱ ሁኔታ የደረሰበትን ሁኔታ በመገምገም በቀሪ ሥራዎች ላይ ምክክር መደረጉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማኅበር የደሴ ሙዚየም ፕሮጀክት ማናጀር አድማሱ አበበ (ዶ.ር) ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ወደ ቅርስ ጥገና ማምጣት መቻሉ እንደ ትምህር መወሰድ ያለበት ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። የደሴ ከተማ የሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ያሉባት ከተማ እንደመኾኗ የግቢውን መልክዓ ምድር ያገናዘበ የማስዋብ ሥራ እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ የቅርስ ባላደራ ማኅበር ዋና ሥራ አሥኪያጅ መቆያ ማሞ የተጎዱ ቅርሶች ቅርስነታቸውን ሳይለቁ እንዲጠገኑ እና በሀገር በቀል ዝርያዎች አካባቢውን የማልማት ሥራ ለዓመታት ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል። የደሴ ሙዚየም በደረሰበት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ጉዳቶች ሳቢያ ለመጠገን ታቅዶ ብሪትሽ ካውንስል ካልቸራል ፕሮቴክሽን ፈንድ ከተሰኘ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ጥገናው ተጀምሮ አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል።

የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስም ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ 90 በመቶ የሚኾነው የሙዚየሙ የጥገና ሥራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ነባር ይዘቱን ሳይለቅ መሠራቱን አንስተዋል።

ለወለሉ ሥራ የሚያስፈልገውን የሀበሻ ፅድ ለማግኘት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንዳለ ገልጸው የሙዚየሙ ቀሪ ሥራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚሠራም ነው የተናገሩት። ዕድሳቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የተዘረፉ ቅርሶችን የማስመለስ ሥራ ይሠራል ያሉት ምክትል ኀላፊው ለዚህም ማኅበረሰቡ እና የሃይማኖት አባቶች ቅርሶቹን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

ተመሳሳይ ቅርሶችን ከማኅበረሰቡ በመፈለግ እና ከሌሎች ሙዚየሞች በማስመጣት ሙዚየሙን ሙሉ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:-መስዑድ ጀማል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሚኮ በቴክኖሎጂ እመርታ ጎዳና እየተጓዘ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ተገልጋዮች ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)