ሰው ተኮር ልማቶች ላይ አተኩሮ መሥራት ተችሏል።

17

ጎንደር: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዞን መሪዎች እና የወረዳ አሥተባባሪ ኮሚቴ መሪዎች የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ቅድመ መደበኛ ጉባኤ እያካሄዱ ነው። ጉባኤው ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የተሠሩ ሥራዎችን ለመገምገም እና የቀጣይ ዓመት ቅድመ ጉባኤ አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርጓል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ ፓርቲው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የገጠሙትን ችግሮች መሻገር የቻለ ስለመኾኑ ተናግረዋል። ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ሥራ የተገባበት ጊዜ መኾኑንም ገልጸዋል። ፓርቲው ሰው ተኮር በኾኑ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሕዝብን ችግር እየፈታ ያለ ነው ብለዋል።

ችግሮችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በተደረገው ጥረት የዲፕሎማሲ የበላይነት መያዝ እንደተቻለም ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት ፓርቲው መሥራቱን ገልጸዋል። በቀጣይም በሕዝቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር የልማት እና የሰላም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችል ብቁ ፓርቲ እንዲኾን ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ፓርቲው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሀገርን ከመፍረስ ታድጓል ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ እና ከውጭ የገጠሟትን ፈተናዎች ከሀገር ወዳድ ሕዝቡ ጋር በመኾን ማለፍ ተችሏልም ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ከተሞች እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ የማይቻል የሚመስል ነገርን እንደሚቻል ካሳየንባቸው ተግባሮች ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም በቱሪዝም መስኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። የበጋ ስንዴ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። የጤና ተቋማት ተደራሽነት ማስፋት እና የጤና መድኅን ተጠቃሚነት ከፍ እንዲል ልዩ ልዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ተደራሽነት እና ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ መኾኑን የጠቀሱት አቶ አወቀ የተማሪዎች ምገባ እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ለትምህርት መስኩ የተሰጠውን ትኩረት ማሳያ መኾኑን አንስተዋል። የፓርቲውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከፍ ለማድረግ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 35 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላት እና ፓርቲውን ከሚደግፉ አካላት መሠብሠቡንም አስታውቀዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 69 ሺህ አባላት በሁለት ዓመት ተኩል ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ኾኖም በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ፓርቲውን የፈተኑ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አቶ አወቀ ተናግረዋል ። ገዥ ትርክትን በሚፈለገው ልክ መገንባት አለመቻሉ ፈታኝ ኹኔታን ፈጥሯልም ነው ያሉት። ፓርቲው ላይ ወጥ የኾነ አቋም አለመያዝ ሌብነት እና ብልሹ አሠራር ፈታኝ ኹኔታዎች ነበሩ ሲሉ ገልጸዋል።

በቀጣይ እነዚህ ችግሮችን ለመሻገር ሁሉም የብልጽግና ፓርቲ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። በጉባኤው በፓርቲው ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የተሠሩ ሥራዎችን የሚያሳዩ እና መሰል ሰነዶች ቀርበዋል።

ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከቡግና ወረዳ በተጨማሪ የላስታ፣ የመቄት፣ የጋዞ እና የአንጎት ወረዳ ነዋሪዎች የዕለት እርዳታ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።
Next article“አሚኮ በቴክኖሎጂ እመርታ ጎዳና እየተጓዘ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)