
ወልድያ: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የሴፍቲኔት፣ የምግብ እርዳታ ሥራዎች እና በተለይም በቡግና ወረዳ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥቷል።
በዞኑ 315 ሺህ 168 የሴፍትኔት ተጠቃሚ ሰዎች እንዳሉ የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አለሙ ይመር በመግለጫቸው አስታውቀዋል። ለእነዚህም 175 ሚሊዮን 718 ሺህ 790 ብር ለግማሽ በጀት ዓመት የተመደበ ሲኾን እስካሁን 157 ሚሊዮን 375 ሺህ 131 ብር ለተጠቃሚዎች ደርሷል ብለዋል።
ለቡግና ወረዳ የተመደበውን 18 ሚሊዮን ብር 6 ሺህ 54 ለሚኾኑ አቅም የሌላቸው ሰዎች መድረስ እያለበት በአካባቢው ባንክ በመዘጋቱ በታለመለት ወቅት ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም ነው ያሉት።
በወረዳው ከ109 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት ኀላፊው እስካሁን በመንግሥት በኩል አራት ሺህ 100 ኩንታል የምግብ እህል ደርሷል፤ እንዲሁም መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች 1 ሺህ 493 ኩንታል የምግብ እህል እና 2 ሺህ 834 ሊትር ዘይት መቅረቡን ገልጸዋል። ይህም ለ27 ሺህ 333 ሰዎች ተደራሽ ኾኗል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከተረጅ ወገኖች ብዛት እና ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ የደረሰው ድጋፍ በጣም ዝቅተኛ በመኾኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዕለት እርዳታ አኳያ እንደ ዞን 168 ሺህ 851 ኩንታል ስንዴ ለ112 ሺህ 517 ሰዎች ባለፉት ስድስት ወራት ተሰራጭቷል። በቡግና ወረዳ ለተከሰተው የምግብ እጥረት እየቀረበ ያለው ድጋፍ ግን በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል።
የቡግና ወረዳ ተረጅ ወገኖች የዕለት እርዳታ በተስፋ እየተጠባበቁ በመኾኑ መንግሥት እና ረጅ ድርጅቶች ድጋፉን ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊያደርሱ እንደሚገባ አሳስበዋል። በዞኑ ከቡግና ወረዳ በተጨማሪ የላስታ፣ የመቄት፣ የጋዞ እና የአንጎት ወረዳ ነዋሪዎችም የዕለት እርዳታ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!