የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ(ደ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት፦

41

ባሕር ዳር: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ዓለም አቀፉ የፔትሮል ዋጋ መረጃ የጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1.25 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0.805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡

ይህ የሚያመለክተው በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሽጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም ካየነው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ በኬንያ 1.351፣ በሩዋንዳ 1.136፣ በኡጋንዳ 1.299፣ በታንዛንያ 1.127 የአሜሪካን ዶላር በሊትር በተመሳሳይ ወቅት እየተሸጠ ይገኛል፡፡

እጅግ ደሃ በሚባሉት እንደ ማላዊ በ1.459፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብልክ 1.746 የአሜሪካን ዶላር በሊትር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከ1.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መኾን የእግር እሳት የሚኾነባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባራቸው ተጠምደዋል። እነሱ የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም።

ራሳቸውን ለሕዝቡ አሳቢ እና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለሕዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው ያቀርባሉ። ይህን የሚያደርጉት እዉነታዉን ስለማያዉቁ ሳይሆን ድብቁ ባሕሪያቸው እንዳይገለጥ ነዉ። ተሳስተዉ እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለዉ በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በኅብረተሰብ መካካል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን አያነሱም፡፡ ለምን ቢባል ይህ ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጠራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሀሳብ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡

እነሱ ይህ የላቸዉም፡፡ በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቻዉ አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጠል እኩይ ፍላጎታቸዉን ማሳካት ነዉ፡፡ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነዉ፡፡ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግሥት ሚና ሚዛን መጠበቅ መኾኑ ለነሱ ምንም ነዉ።

በነጻ ገበያ ዉስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ሥርዓት መንግሥት እንዲያደርግ የማይገደድባቸዉ ጉዳዮችን በማንሳት መንግሥትን ይከሳሉ፡፡ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም። መንግሥት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማኅበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል። በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል።

ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የኅብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ይረዳል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድኃኒት እና መሰል የጤና ጉዳዮች ከፍተኛ የሚባለውን ድጎማ እያደረገ ነው። በዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ያደርጋል። መንግሥት መደበኛ ተግባራትንም ያከናውናል።

ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የኾኑ እና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ ነው። በተለይም የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ትሩፋት ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ነው። የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው። የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታ እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ሥራም ተጀምሯል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ ነው። ሕዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መኾኑን በቅርቡ በሚኒስትሮች ደረጃ በሁሉም ክልሎች የተደረገው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አረጋግጧል።

መንግሥት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየኾነ ነው። እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል። አጋጣሚዉን በመጠቀም ኅብረተሰቡ ላይ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ኅብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛዉንም አይነት ድርጊቶች እየተከታተለ ርምጃ ይወስዳል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለዘመናት ከልማት ርቃ የነበረችው ጎንደር ከተማ የልማቱ ተጠቃሚ እየኾነች ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው
Next articleከቡግና ወረዳ በተጨማሪ የላስታ፣ የመቄት፣ የጋዞ እና የአንጎት ወረዳ ነዋሪዎች የዕለት እርዳታ በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ።