“የዘንድሮው የልደት በዓል ቱሪዝሙን ወደነበረበት ለመመለስ የተስፋ ብርሃን የቀደደበት ነው” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር

19

ወልድያ: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ እንግዳ ናፍቀው ለከረሙ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች በርካታ እንግዶችን ያሳየ ነው። ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ ታላቅ ተስፋም የሰጠ ነው።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ላሊበላ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግረዋል። በምጣኔ ሃብትም ለሀገር ያላት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው ብለዋል። ከኮሮና ቫይረስ በፊት እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ይመጡባት እንደነበር ነው ያስታወሱት።

በውጭ ምንዛሬም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይደረግባት የነበረች ከተማ መኾኗን ነው የተናገሩት። ላሊበላ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታደርግ ከተማ ናት ብለዋል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም ላይ መሥራት ከቻሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ይመለሳል ነው ያሉት።

ሰላም ከተረጋገጠ የቱሪዝም ሃብቱ ከፍ እንደሚልም ገልጸዋል። የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከኮሮና ቫይረስ በፊት እንደነበረው ኾኖ ቢቀጥል ኖሮ የአካባቢው ምጣኔ ሃብትም በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ይል እንደነበር ነው ያመላከቱት። በቱሪዝሙ ላይ በደረሰ ጉዳት ግን ማኅበረሰቡ ለችግር ተጋልጦ ኖሯል ነው ያሉት።

የዘንድሮው የልደት በዓል የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደነበረበት እንደሚመለስ አመላካች ነው ብለዋል። በልደት በዓል በርካታ ወገኖች ለሥራ መነሳሳታቸውን እና ገቢ መሠብሠባቸውንም ተናግረዋል። የልደት በዓል የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች የዓመት ጉርሳቸውን የሚሠበሥቡበት ነው ብለዋል።

የውጭ ሀገር ጎብኝዎችም ብቻ ሳይኾን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችንም ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ነው የተናገሩት ። በልደት በዓል ትልቅ የቱሪዝም ተስፋ መመልከታቸውንም ገልጸዋል። ቱሪዝም ላይ መሥራት ከተቻለ እንደሀገር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት።

ልደት ለላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ ልዩ ነው የምንለው በምክንያት ነው ያሉት ኀላፊው ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሕልውናውም መኾኑን ነው የተናገሩት። የዘንድሮው የልደት በዓል ቱሪዝሙን ወደነበረበት ለመመለስ የተስፋ ብርሃን የቀደደበት ነው ብለዋል።

ጥምቀትን በድምቀት ማክበር ደግሞ የበለጠ ተስፋውን ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት። የታየውን ተስፋ የበለጠ ዕውን ለማድረግ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሰላምን፣ አንድነትን እና አብሮነትን ማስተማር አለባቸው።
Next article“ለዘመናት ከልማት ርቃ የነበረችው ጎንደር ከተማ የልማቱ ተጠቃሚ እየኾነች ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው