በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ሁሉም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

76

አዲስ አበባ: ጥር 01/2027 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር በ2017 ዓ.ም የጤናማ እናትነት ወር ዝግጅት እና አከባበር ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ጤናማ የእናቶች ወር “ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናቶች፣ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚከበር ጠቅሰው በጥር ወር በዓለም ለ38ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል ብለዋል።

የእናቶችን ጤና መጠበቅ እና በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ሞት መቀነስ በዚህ ወር ብቻ ሳይኾን የዘወትር ሥራ መኾን ይገባዋል ብለዋል። የጤና ሚኒስቴርም የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እና ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ጤና ኬላዎችን እና ጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

በወሊድ ጊዜ በደም መፍሰስ ምክንያት እናቶች ሕይወታቸውን እንዳያጡ የደም ባንክ ቅርንጫፎችን ወደ 53 በማሳደግ የደም እጥረት እንዳያጋጥም በሥራ ላይ ነን ብለዋል። ሚኒስትሯ ለጤና ባለሙያዎች በሁሉም የጤና ዘርፎች ብቁ እንዲኾኑ ሥልጠናዎችን በመስጠት ጤናማ እናትነት ለሁሉም እንዲኾን እየሠራን ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥር መቀነሱን ሚኒስተሯ ገልጸው አሁንም እናት በወሊድ ምክንያት እንዳትሞት ሁሉም ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በልደት በዓል የታየውን የቱሪዝም ተስፋ ለማስቀጠል ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል” የቅዱስ የላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝ ማኅበር
Next articleየኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሰላምን፣ አንድነትን እና አብሮነትን ማስተማር አለባቸው።