“በልደት በዓል የታየውን የቱሪዝም ተስፋ ለማስቀጠል ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል” የቅዱስ የላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝ ማኅበር

26

ወልድያ: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች የአካባቢው ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ከፍተኛ የቱሪዝም መዳረሻዎች ናቸው። ሀገር ሰላም በኾነ ጊዜ በርካታ እንግዶች ወደ አካባቢው ይገባሉ። የአካባቢው ማኅበረሰብም ከጎብኝዎች በሚያገኘው ገቢ ሕይወቱን ይመራል። ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ችግር ገጥሞት ከርሟል። የቱሪዝም እንቅስቃሴ በመጎዳቱ ደግሞ ገቢያቸው በቱሪዝሙ ላይ የተመሠረቱት ወገኖች ተጎድተዋል።

የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው የቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር ሊቀ መንበር እስታሉ ቀለሙ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ትሩፋት አላቸው ብለዋል። በርካታ እንግዶች አብያተክርስቲያናቱን ለመጎብኘት ይመጡ እንደነበርም አስታውሰዋል። የልደት በዓል ሲኾን ደግሞ እንግዶች በስፋት እንደሚመጡ ነው የተናገሩት ። ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩት ተደጋጋሚ ችግሮች ግን እንግዶች በከፍተኛ መጠን መቀነሳቸውን ነው የገለጹት።

በማኀበራቸው 165 አስጎብኝዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሊቀ መንበሩ ባለፉት ጊዜያት በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት አስጎብኝዎች በችግር ውስጥ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል። ቀደም ሲል 200 የሚደርሱ አስጎብኝዎች እንደነበሯቸው ነው የተናገሩት። ነገር ግን ብዙቹ ችግርን ለመሸሸ ተሰደዋል። ተደራራቢ ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ቅዱስ ላሊበላ ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቱሪዝም ብቻ ይተዳደር የነበረው የአካባቢው አስጎብኝ እና ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ ቆይቷል ነው ያሉት። የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት የቱሪዝም ባለቤቱን ማነቃቃት፣ የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። ሰላሙን ካረጋገጡ በኋላ እንግዶች እንዲመጡ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት። የአካባቢው ሰላም ከተረጋገጠ እና የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ ካገኙ ጎብኝዎች በስፋት ይመጣሉ ብለዋል።

አስጎብኝዎች ብቸኛ ሥራቸው ማስጎብኘት ብቻ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ የቱሪዝም እንቅስቃሴው አደጋ ላይ ሲወድቅ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፣ መጪው ጊዜ የተሻለ እንዲኾን ቱሪዝሙን ማነቃቃት ይገባል ነው ያሉት። ከፍተኛ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው አስጎብኝዎች መደገፍ አለባቸው ብለዋል።
በልደት በዓል የመጡ እንግዶች ቱሪዝሙን የተሻላ እንዲኾን እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ አንስተዋል።

የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው ቱሪስት አስጎብኝ ማኅበር ጸሐፊ ሻምበል ካሳ ኃይሌ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ አስጎብኝዎቻችን ተበትነውብናል ነው ያሉት። የሚበሉት እስኪያጡ ድረስ ተቸግረው እንደቆዩም አንስተዋል። ቤተሰብ ማሥተዳደር ተቸግረው የተሰደዱ መኖራቸውን ነው የተናገሩት ። የአካባቢውን ባሕል፣ ሃይማኖት እና ታሪክ የሚረዱ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚችሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ድንገተኛ በመኾኑ የተዘጋጀ ሰው እንዳልነበርም አንስተዋል።

ከችግር ለመውጣት መፍትሔው ሰላም ነው፣ በንግግር ማመን፣ ሁኔታዎችን መረዳት እና በውይይት ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የልደት በዓል ለቱሪዝሙ መነቃቃት ትልቅ ተስፋ ጥሎላቸው እንዳለፈም ገልጸዋል። በርካታ እንግዶች ይመጣሉ ብለው አስበው እንዳልነበረ የተናገሩት ጸሐፊው በበዓሉ በርካታ እንግዶች በመምጣታቸው መደሰታቸውን ነው የተናገሩት ። በዚህ ከቀጠለ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንደሚጨምር ያላቸውን ተስፋ እና እምነት ገልጸዋል።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ በቱሪዝሙ በደረሰው መቀዛቀዝ አስጎብኝዎች እና ቤተክርስቲያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የተናገሩት። የአካባቢው ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ ምንጩ ቱሪዝም መኾንም አንስተዋል። ችግሮችን ለመቋቋም በከተማ አሥተዳደሩ፣ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከተማ አሥተዳደሩ በቻለው መጠን ለአስጎብኝዎች ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

ችግሩ እንዲያልፉ እና ቢያንስ የዕለት ምግብ እንዳይቸገሩ የማድረግ ሥራ መሥራታቸውን ነው የተናገሩት። የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት እንዲመለስ በዓላቱን በድምቀት ማክበር ያስፈልጋል ነው ያሉት። የልደት በዓልም በድምቀት መከበሩን ነው የተናገሩት። የጥምቀት በዓልንም በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። አሁን ያለው መነቃቃት በዚሁ የሚቀጥል ከኾነ የቱሪዝም ገቢውም እንደሚያደርግ ነው ያመላከቱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከውድድር ውጭ አድርጎን ቆይቷል” የሆቴሎች ማኅበር
Next articleበወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ሁሉም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።