
ወልድያ: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ላሊበላ በሰላም ጊዜ የጎብኝዎች መዳረሻ ናት። የአካባቢው ማኅበረሰብም የሕይዎት መሠረቱ ቱሪዝም ነው። ሰላም በታጣ ጊዜ ግን ቱሪዝም ይቆማል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ሕይወትም ይናጋል። በከተማዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች አሉ። በሰላም ጊዜ በርካታ እንግዶችን ይቀበላሉ። ለአካባቢው ወጣቶችም የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። የሰላም እጦት ግን ሁሉ ነገር እንዲናጋ አድርጎት ቆይቷል።
የቅዱስ ላሊበላ ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የመዘና ሪዞርት ባለቤት ዮሐንስ አሰፋ በማኅበራቸው ውስጥ 52 ሆቴሎች እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሆቴሎቹ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ በተደጋጋሚ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የሆቴል ባለሀብቶች ከሥራ ውጭ ኾነዋል ነው ያሉት። አብዛኛዎቹም አካባቢውን ለቀው ለመሄድ ተገድደዋል ብለዋል።
ሆቴሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እንደነበሯቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና እርሱን ተከትሎ በመጣው የሥራ ማጣት ምክንያት ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን ቀንሰዋል ነው ያሉት። እንግዳ የማያጡ የነበሩ ሆቴሎች ለሳምንታት ምንም አይነት እንግዳ ሳያገኙ ይቆዩ እንደነበር ነው የተናገሩት።
በልደት በዓል የተወሰኑ ሠራተኞቻቸውን መመለሳቸውን ገልጸዋል። እንግዳው የሚቀጥል ከኾነ ሠራተኞቻችንም ይቀጥላሉ። ያ ካልኾነ ግን ያለ ሥራ ሠራተኛ ይዞ መቀጠል አደጋ ነው ብለዋል። ላለፉት ዓመታት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጎድቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሆቴሎች ደግሞ ብድር ያለባቸው መኾናቸውን ነው የገለጹት። ባንኮች ብድራቸውን ይቆጥራሉ እኛ ግን የምንከፍለው የለንም ነው ያሉት።
የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲጨምር ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። የላሊበላን ችግር ሁሉም እንደሚያውቅ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ችግር የኾነው መፍትሔ የሚወስድ መጥፋቱ ነው ብለዋል። ሠርተን እንድንከፍል የእፎይታ ጊዜ ሊሰጠን ይገባል ነው ያሉት። ሰላሙ ከመጣ ሠርተው እንደሚከፍሉትም ተናግረዋል። ሰላም ካለ ቅዱስ ላሊበላ በሰጠን ሃብት ሠርተን ለመክፈል አንቸገርም ነው ያሉት።
የዛን ስዩም ሆቴል ባለቤት አበበ ደምሳሽ ቱሪዝሙ በተደጋጋሚ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል ብለዋል። በሰሜኑ ጦርነት ደግሞ ሆቴሎች ተዘርፈው እንደነበር ነው የተናገሩት። የደረሰው ዘረፋ ተጠንቶ ለሚመለከተው አካል መሰጠቱን ነው የገለጹት። ገቢዋ ቱሪዝም ብቻ ለኾነችው ከተማ የቱሪዝም መቆም ጉዳቱን ከፍተኛ አድርጎታል ነው ያሉት። ቱሪዝም ያለ ሰላም እንደማይታሰብም ገልጸዋል።
በጸጥታው ችግር ምክንያት ሥራችን ቆሞ ቆይቷል፣ ከውድድሩ ውጭ ኾነንም ከርመናል፣ ገቢያችን ቆሟል፣ ለባንክ እዳ ተጋላጭ ኾነናል ብለዋል። ከነበሯቸው ሠራተኞቻቸው መካከል አብዛኛዎቹን መበተናቸውንም ገልጸዋል። ያለ ወለድ የረጅም ጊዜ እፎይታ እንዲሰጣቸውም ተናግረዋል። አሁን ያለው የጸጥታ ችግር በሰላም እና በውይይት ካልተቋጨ የባሰ ችግር ውስጥ እንገባለን ነው ያሉት። የባሰ እና የተወሳሰበ ችግር ከገባን በኋላ መፍትሔ ቢመጣ እንዳልመጣ ይቆጠራል ብለዋል። የሕዝብን ሰቆቃ በመረዳት ፈጥኖ ወደ ሰላማዊ ውይይት መግባት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የልደት በዓል በአካባቢው ደምቆ በመከበሩ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ተስፋ እንደሰነቁበትም ገልጸዋል። ግጭቱን በሰላም የመፍታት ሂደት ካለ ደግሞ ተስፋችን የበለጠ ዕውን ይኾናል ነው ያሉት። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ላሊበላ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኗን ገልጸዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው ተደጋጋሚ ችግር የቱሪዝም መቀዛቀዝ በመኖሩ ምክንያት ሆቴሎች ለሥራ ተቸግረው ቆይተዋል ነው ያሉት። ሆቴሎች ከብድር ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል። ችግሮችን ለመፍታት መጀመሪያ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ወደነበረበት መመለስ ይገባል ነው ያሉት። ቱሪዝሙ ወደነበረበት ከተመለሰ ሆቴሎች ሠርተው መመለስ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ውድመት የደረሰባቸውን ሆቴሎች ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አስጠንተው ለሚመለከተው አካል መስጠታቸውንም ተናግረዋል። የተደረገው ጥናት ላሊበላ ላይ የደረሰው የቱሪዝም ጉዳት ምንድን ነው?የሚለውን የሚያመላክት መኾኑን ነው ያመላከቱት።
ባለሀብቶች የሚፈልጉትን ነገር ለማሟላት እየጠየቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ታላላቅ የሥራ ኀላፊዎች ጉዳቱን በአካል እንዲያዩት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። በሰላም ምክንያት የተረበሸውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመመለስ ሁሉም የሰላም ባለቤት መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!