“አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተናግዳቸው ዘገባዎች የሕዝቦችን ትስስር የሚያጠናክሩ ናቸው” የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም ገነሞ

42

ባሕር ዳር: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ እና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ ለመኾን ራሱን በቴክኖሎጅ እያጠናከረ ይገኛል። ዛሬም ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ቴክኖሎጅን አስመርቆ ወደ ሥራ አስገብቷል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ዘላለም ገነሞ እንዳሉት አሚኮ በተለያዩ ሚዲየሞች እና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተናግዳቸው ዘገባዎች የሕዝቦችን ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው። የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በበርካታ የብሔረሰብ ቋንቋዎች እንደሚያሰራጭ ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው አሚኮም ለብዝኀነት ትኩረት ከሰጡ ሚዲያዎች አንዱ እንዲኾን አድርጎታል ብለዋል።

ይህ ደግሞ የማኅበረሰቡን ግንኙነት ያስተሳስራል፤ የሕዝቦችን በጋራ የመልማት ፍላጎት ያሳድጋል ነው ያሉት። አሁን ላይ አሚኮ የታጠቀው ቴክኖሎጅም ከሀገር አቀፍ አልፎ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ ለመኾን ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት። ቴክኖሎጅውን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የክልሉን ሃብት፣ ባሕል እና እሴት ማሳወቅ ይገባልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ባለሙያ እንግዳው ከፍያለው እንዳሉት አሚኮ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የክልሉ ሕዝብ ድምጽ ኾኖ በትጋት እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው። በተለይም ደግሞ የክልሉ የምጣኔ ሃብት መሠረት የኾነው የግብርና ዘርፍ ላይ የሚሠራው ሥራ ማኅበረሰቡ በምግብ ራሱን እንዲችል አቅም የሚፈጥር ነው።

አሁን ላይ የታጠቀው ቴክኖሎጅ ደግሞ በክልሉ የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ሌሎች ሁነቶችን ከቦታው ኾኖ ለማሰራጨት ያግዛል፤ ይህም የሙያተኞችን ድካም በመቀነስ መረጃን በፍጥነት እና በጥራት ለማሰራጨት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የባሕር ዳር ማዕከል ባለሙያ ደሳለኝ ቢራራ እንዳሉት አሚኮ ለክልሉ ሕዝብ የሚተጋ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን እያዘመነ የመጣ ሚዲያ ነው፤ አሁን የታጠቀው ቴክኖሎጅ ደግሞ የማኅበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እና በክልሉ ያለውን እምቅ ባሕል፣ ወግ እና እሴት ሌሎች የሀገሪቱ እና የዓለም ሕዝብ እንዲያውቃቸው ለማድረግ አቅም የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቦርከና ወንዝ የተገነባው ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next article“አሚኮ አዲስና ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ማሰራጫ ስቱዲዮ መጠቀሙ የሚዲያውን የላቀ ከፍታ ለማሳየት እድል ይፈጥርለታል” የአማራ ክልል ምክር ቤት