
ደሴ: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ በመደበው በ53 ሚሊዮን ብር በቃሉ ወረዳ ቦርከና ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት ነዋሪዎቹ መካከል የ032 ቀበሌ ነዋሪ ይማም እንድሪስ ወንዙ የቤተሰቦቻችንን ሕይወት ሲቀጥፍ ኖሯል፤ አሁን ድልድይ መሠራቱ ችግሩን ይቀርፋል ብለዋል። በተጨማሪም የግብርና ምርቶችን እንደልብ ወደ ገበያ እንድናወጣ ያስችለናል ነው ያሉት። የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ ኢብራሂም አሰን የኅብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መልስ ያገኘበት መኾኑን ጠቅሰዋል። የድልድዩ ግንባታም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው የላቀ እንደሚኾን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) የድልድይ ግንባታው 53 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት ተናግረዋል። የድልድዩ መገንባት አንድም ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ እድል በመፍጠር፣ በሌላ በኩል የአካባቢውን ማኅበረሰብ የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ሰላም መኾን ለፕሮጀክቱ ግንባታ መሳለጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል። በክልሉ የተለያዩ የመንገድ እና የድልድይ ሥራዎችን በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በቦርከና ወንዝ ላይ የተገነባው 50 ሜትር ርዝመት ያለውን ድልድይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች ልዑክ በተገኙበት ነው በዛሬው እለት የተመረቀው።
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
