
ባሕር ዳር: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ የተንቀሳቃሽ ማሰራጫ ስቱዲዮ ዛሬ መጠቀም ጀምራል፡፡ በዚህ የማሰራጫ ስቱዲዮ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እና የአሚኮ የቦርድ ሰብሳቢ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ ለሕዝብ ዕድገት እና ብልጽግና የሚሠራ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ ይህም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡
መንግሥትም ኾነ ሕዝብ የጋራ እና የወል ትርክት እንዲገነባ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ቋንቋ እና ማንነት ያለባት ሀገር ስለመኾኗም አስረድተዋል፡፡ የአማራ ክልል ባለብዙ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መስተጋብሮች ባለቤት እንደኾነ የተናገሩት አቶ ይርጋ ሲሳይ ይህን የክልሉን አቅም አውጥቶ በመጠቀም ረገድ አሚኮ የተጫዎተው ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በትብብር እና ትስስር ብሎም በአንድነት ቆሞ ሚዲያው ከሠራ ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡ አሚኮ ወሳኝ ተቋም ነው የሚባለው ክልሉ ያለውን የበለጸገ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሃብት አውጥቶ መጠቀም የሚያስችል በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡ አሚኮ አሁን እየታየ ያለውን ልማት በማቀጣጠል ብሎም የሚገጥሙ ችግሮችን በመፍታት እየተጫዎተ ያለው ሚና ከፍተኛ የሚባል እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
አሚኮ የተጀመሩ የስንዴ፣ የእንሰሳት ሃብት፣ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎችን እና ሌሎችንም የክልሉ ሃብቶች ወደ ገበያ በማቅረብ አሚኮ ያለው ድርሻ የማይተካ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ በተለይም አሁን ላይ የገጠመውን የሰላም ችግር ተረድቶ ክልሉ እና ሀገርን ከአደጋ ለመጠበቅ የተጫወተው ሚና እና ያለፈበት አጣብቂኝ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ነው ያሉት፡፡
የአሚኮ ባለሙያዎች አሁን ላይ በችግር ተፈትነው ያለፉበት ወቅት እንደኾነ የተናገሩት አቶ ይርጋ አሚኮ የክልሉ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ የተጫዎተው ሚና ከፍ ያለ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡ አሚኮ አሁንም ቢኾን ክልሉ ሰላሙን አረጋግጦ የተሻለ ልማት እና ብልጽግናን እንዲያረጋግጥ ከፍ ያለ ኀላፊነት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ላይ ሀገራት አሸናፊ የሚኾኑት ተወዳድረው እና ተገዳድረው መቆም ሲችሉ ብቻ እንደኾነም አቶ ይርጋ ገልጸዋል፡፡ ገዥ ትርክትን ማስረጽ የሚቻለው ጠንካራ የሚዲያ ተቋም መገንባት ሲቻል እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ ዓለም ወደ ዲጂታል መሥመር በፍጥነት እየተጓዘች እንደምትገኝ እና ሁሉም ነገር በዲጂታል የሚከወን በመኾኑ በዲጂታሉ ዘርፍ የሠለጠኑ ሙያተኞችን እና አመራር ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድም አሚኮ ጠንካራ ሥራ እየሠራ ቢኾንም የበለጠ ጠንክሮ እንዲወጣ ሊሠራ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ አሚኮ ጠንካራ ተቋም ለመመስረት በሪፎርም እያለፈ ያለ ተቋም ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡ አሚኮን ምሳሌ የሚኾን ተቋም አድርጎ ለመቅረጽ ያለው መደጋገፍ እና መተጋገዝ ከፍ ያለ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡
አሚኮ በጥራት እና ተደራሽነት በኩል የተሻለ ለመሥራት ብዙ ርቀት እየተጓዘ የሚገኝ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡ አሚኮ ዋና መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ ቅርንጫፍ ጣቢያዎቹ ላይ ለማስፋት ያለው ጅምር ከፍ ያለ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ በተለይም አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ለመጠቀም እየሠራ ያለው ሥራ እጅግ የላቀ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡
አሚኮን ከክልሉ እና ከሀገር ባለፈ በቀጣናው ተደማጭ የሚኾን ሚዲያ አድርጎ ለመሥራት ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ለማገዝም ከክልል እስከ ፌደራል ድረስ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግለት አስረድተዋል፡፡ በፈተና ተፈትኖ የሚወጣ እና ጠንካራ እና ችግርን ተሻግሮ ሀገር የሚያሻግር ባለሙያ በአሚኮ ውስጥ መፈጠሩን አንሥተው ለዚህም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
አሚኮ በቴክኖሎጅ እንዲደረጅ ለማድረግ አቋም ተይዞ እጅግ ያደገ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በሰጠው ትኩረትም አሚኮ የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ (ኦቢቫን) ተጠቃሚ እንዲኾን መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡ አሚኮን ሁሉም የሚያምነው እና እንደምሳሌ የሚጠቀስ ተቋም እንዲኾንም በትጋት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!