
ባሕር ዳር: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስቱድዮ ቴክኖሎጂ ገዝቶ መጠቀም ጀምሯል። በዚህ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስቱድዮ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ ሚዲያ ከተለመደው መረጃ የመስጠት እና የማስተማር ሚናው በላይ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ለልማት ሰፊ ሚና ይጫዎታል ብለዋል።
የሕዝቦችን ተሳትፎ እና መልካም አሥተዳደርን በማረጋገጥም አሚኮ ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ኮርፖሬሽን የአየር ሰዓት ገዝቶ ይጠቀም ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ኅብረተሰቡን ሲያገለግል መቆየቱን እናውቃለን ነው ያሉት።
በሀገራችን ከመልክዓ ምድር፣ ከቋንቋ እና ከማንነት ጋር ተያይዞ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በጋዜጣ ተደራሽ ያልኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ይህንን ችግር የተገነዘበው አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች ሽፋኑን አሳድጎ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስለኾነ የሚመሰገን ነው ብለዋል። በክልሉ በተለይ በሬድዮ በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈትም ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በቴሌቪዥንም በሳተላይት መቶ በመቶ ሽፋን በመስጠት ወደ ውጪ ሀገር ጭምር የሚዳረስ ስርጭት እያደረገ መኾኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የስፖርት ውድድሮችን ከኬንያ በኪራይ እያመጣን እና ዶላር እየከፈልን ነበር የምንጠቀመው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ “አሚኮ ይህንን መሣሪያ በመታጠቁ ለሕዝቡ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ወጭንም” ያድንልናል፤ ለራሱም ገቢ ያስገኛል ብለዋል።
በአማራ ክልል በርካታ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን መረጃ ቀርጾ በማሰራጨት እና ለትውልድም በታሪክነት ለማስቀመጥ የሚጠቅም መሣሪያ በመኾኑ ትልቅ የሀገር ሐብት ነው። አሚኮ ይህንን መሣሪያ በቁርጠኝነት በመታጠቁ በባለሥልጣኑ ስም እናመሰግናለን ብለዋል። በቀጣይም ለአሚኮ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!