“አሚኮ የበለጠ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ይተጋ ዘንድ፣ ይህ ቴክኖሎጅ ይገባዋል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

25

ባሕር ዳር: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘመኑ የደረሰበትን የተንቀሳቃሽ የቴሌቪዥን የቀጥታ ማሰራጫ መሣሪያ በዛሬው ዕለት አስመርቆ አስጀምሯል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) አሚኮ እንደመሪ ቃሉ ሁሉ ለኅብረተሰብ ለውጥ ሲተጋ የቆየ ተቋም ነው ብለዋል።

በችግሮች ውስጥም ኾኖ በርካታ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጠቃሚ ተግባራትን ሲሠራ የቆየ ተቋም እንደኾነ ገልጸዋል። አሚኮ ከተሞች ለውጥ እንዲያመጡ ሲተጋ የቆየ እና የሕዝቦች አንደበት በመኾን በኩልም ሊዘነጉ የማይገቡ ተግባራትን ሲከውን የቆየ ትልቅ የሕዝብ ተቋም ነው ብለውታል።

ተቋሙ አሁን ላይ አድማሱን ለማስፋትም ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጅ እየታጠቀ ይገኛል ነው ያሉት። አሁን የተመረቀው የኦቢ ቫን ቴክኖሎጅም ከዓለም አቀፍ ቴክኖሎጅ ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው እንደኾነ ተናግረዋል። በቀጣይም “አሚኮ የሕዝቦችን አንድነት እና ወንድማማችነት ለማስተሳሰር በሚያደርገው ጥረት ይህ ቴግኖሎጅ አጋዥ ነው” ብለዋል።

የአሚኮ ሠራተኞች ለሕዝብ ተጠቃሚነት እየሠሩት ባለው ሥራ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል። የአሚኮ ሠራተኞች ተግባራቸውን አጠናክረው የበለጠ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ይተጉ ዘንድ ይህ ቴክኖሎጅ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በቀጣይም ሠራተኞቹ ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጅ ሁሉ እየሠለጠኑ ራሳቸውን ማብቃት እና ማሳደግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ለአብነትም የኮደርስ ሥልጠና እና ሌሎችን ሥልጠናዎች በመውሰድ ራሳቸውን ማብቃት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

አሚኮ በቀጣይ ዘመኑም ለኅብረተሰብ ለውጥ መትጋቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ገቡ።
Next article“አሚኮ የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ባለቤት መኾኑ ለሕዝቡ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ ወጭንም ያድንልናል” የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛ ባለሥልጣን