
ባሕር ዳር: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ (ኦቢቫን) ዛሬ አስመርቋል፡፡ የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ከ30 ዓመታት በፊት በበኩር ጋዜጣ የጀመረው አሚኮ በየጊዜው ማደግን ባሕሉ በማድረግ አሁን ላይ በ12 ቋንቋዎች የሚሠራ ብዝኀ ልሳን ነው ኾኗል ብለዋል፡፡
አሚኮ አሁን በሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎችም ተደራሽ ኾኗል፡፡ ተጨማሪ ጣቢያዎችም እንዲኖሩ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሰቆጣ ኤፍ ኤም በዚህ ዓመት ወደ ስርጭት ይገባልም ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን፡፡ ገንዳ ውኃ ከተማ ላይም ወደ ጎረቤት ሀገር የሚደርስ የራዲዮ ጣቢያ እንዲኖር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አሚኮ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉት ያሉት አቶ ሙሉቀን በኅብር ጣቢያ ከክልሉ ውጭ ያሉ ሕዝቦች ገዥ ትርክትን ለማስረጽ እየሠራ ነው፡፡
አሚኮ በዲጂታል ሚዲያው ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ዘገባዎችን እየሠራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀድሞ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አብሮነትን እንደ ሀገር እየሰበከ የሚገኝ የሕዝብ ሚዲያ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
አሚኮ የሕዝብ ድምጽ ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን የአማራ ሕዝብ ወረራ ሲፈጸምበት ቀድሞ በመድረስ በየግንባሮቹ ዘገባዎችን እንዳደረሰም አስታውሰዋል፡፡
አሚኮ ዜናዎችን ከባሕር ዳር በተጨማሪ ከአዲስ አበባ እና ከደሴ ከተማ እያሰራጨም ይገኛል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!