
ባሕር ዳር: ጥር 1/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራን ውበት፣ ማንነት፣ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ልህቀቱን ሊገልጥ በአርቆ አሳቢዎች ሲመሠረት ብዙዎች አሁን የደረሰበት ደረጃ ይደርሳል ብለው ግን አላሰቡም። የዚያ ዘመን ድንቅ ልጆች ምንም ሳይኖራቸው ብዕር እና ወረቀት አዋድደው ትንሽ የሚመስል ግን ደግሞ የብዙ ድንቅ መሪዎች የአመራር ጥበብ ሊገልጥ የሚችል ድርጅትን መሠረቱ።
እነዛ ሩቅ አሳቢዎች ድንጋይ ላይ ተቀምጠው በወረቀት የክልሉን ገጸ በረከቶች ማንነቶች አጉልተው ማውጣት የጀመሩበት የመጀመሪያ ልጅ በ1987 ዓ.ም በኩር ብለው በሰየሙት ጋዜጣ ነበር። እርግጥ ነው ቀናት እና ወራት እንዲሁም ዓመታት ሲጨምሩ ይህ ሃሳብም አብሮ ማደግ እና መመንደግ ጀምሯል።
ከወረቀት ወደ ድምጽ እና የምስል ሞገድ ይቀየር ዘንድ ሃሳብ መነጨ እንዴት ኾኖ በባዶ ምንም ሳይኖር የሚለው እሳቤ ቢኖርም ይህን እሳቤ የሚሰብር ሃሳብ ብቅ አለ ሥራውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአየር ሰዓት ኪራይ ይሠሩ ዘንድ ሃሳብ ወጠኑ። ይህም ሃሳብ ዕውን ኾነ ተግባሩም የሕዝቡን የተደበቀ ጥበብ፣ ሃብት፣ እሳቤ፣ መገለጫ፣ የሀገር ካስማ እና ማገርነት ተግባር ከዛሬ 30 ዓመት በፊት መግለጥ ጀመረ። ይህ ሁነት ክልሉን በመላው ሀገሪቱ ብሎም በዓለም እንዲታወቅ ትልቅ በርን ከፍቷል።
አዎ አማራ ክልል ትልቅ ክልል ነው፤ ተፈጥሯዊም ኾነ ሰው ሠራሽ ሃብቶች በስፋት ያሉበት፤ ይሁን እንጅ ይህን ትልቅነቱን አውጥቶ ማሳየት መገላለጥ ያስፈልግ ነበር እና እያደገ የመጣው አሚኮ ይህን ዕውነታ ገልጦ አሳይቷል። 30 ዓመታት ቀላል መስለው ቢታዩም አሚኮ በእነዚህ ዓመታት ቀስ እያለ እንደሚያድግ ልጅ ማደግ እና መመንደግ የቻለ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ከኪራይ ሥራ ወጥቶ ራሱን ሲችል ድንቅ ሥራ ተብሎም ነበር።
አሚኮ ግን በሰው ኀይልም ይሁን በቴክኖሎጅ ማደጉን ቀጥሏል። ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለማቀፍ ቋንቋዎች ድረስ በማሰራጨት የሀገር ሃብት እና ሀገር ቀያሪ ተቋምም ተሰኝቷል። ይህን ደግሞ በየዘመናቱ የመጡ መሪዎች መስክረውለታል። አሁን አሚኮ ሀገር የኮራበት ተቋም መኾን ችሏል። አሁን ላይ አሚኮ ሀገሪቱ ካሉ ተቋማት ጋር እየተፎካከረ እና የሀገሪቱ ብሎም የምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ሚዲያ ለመኾን ራዕይ አስቀምጦ እየሠራ ያለ ተቋም መኾን ችሏል።
ለዚህ ደግሞ ራሱን በሰው ኅይል እና በቴክኖሎጅ እያሳደገ ይገኛል። ዛሬ ላይ አሚኮ ዕምነት የሚጣልበት እና በሀገሪቱ ስሙ ቀድሞ ከሚጠሩ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት መካከል ቀድሞ መጠቀስ የቻለው በሥራ እና በውጤቱ ነው። እነኾ ዛሬም ይህ ትልቅ የክልል ብሎም የሀገር መገለጫ የኾነው ተቋም ካለበት ማማ ከፍ ብሎ እያደገ እና እየተመነደገ እንዲሄድ የማያቋርጡ ሥራዎች ቀጥለዋል።
አሚኮ አሁን ላይ ዓለማችን ላይ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ታጥቀውታል የሚባለውን የቀጥታ ስርጭት መምሪያ ኦቢ ቫን ከታጠቁ ሚዲያዎች መካከል አንዱ ኾኗል። ይህ ሁነት እና ተግባር የአሚኮን በረጅም ርቀት መወንጨፍ የሚያሳይ ከመኾኑም በላይ በውስጡ ከሚሠሩ ልጆቹ በተጨማሪ ለክልሉ ሕዝብ ድንቅ ስኬት ነው። ለሀገርም የዕድገት መለኪያ እና ማሳያ ኾኖ ይታያል።
አሚኮ በከፍታ የዕድገት ማማ ላይ ኾኖ መብረሩን ቀጥሏል። ይህን ዕውነት ደግሞ በሌሎች የመገናኛ ብዙኀን ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች የሚጋሩት ዕውነት ነው። የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ከዚህ በፊት ለሚዲያ በሰጡት ሃሳብ አሚኮ አሁን ያለበትን ደረጃ ሲገልጹ አሚኮ በትንሽ እየጀመረ ግን ደግሞ በትልቁ እያደገ ያለ ተቋም ነው ብለውታል።
እንደ ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ገለጻ አሚኮ ሲመሠረት በበኩር ጋዜጣ በአማርኛ ተመሥርቶ አሁን አድጎ እና ተመንድጎ ባለ ብዙ ቋንቋ ባለቤት የኾነ ሚዲያ ነው። ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም ተደራሽ የሚኾንባቸውን ቋንቋዎች አሚኮ መርጦ እየሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል። አሚኮ ይህን በማድረጉ የክልሉን ሕዝብ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ከማስተሳሰር ባለፈ የሀገር ኩራት መኾን የቻለ ተቋም ለመኾን የበቃ ስለመኾኑም ነበር የተናገሩት።
ሲጀመር በትንሹ የተጀመረው አሚኮ አሁን ላይ ሁለት የቴሌቪዥን፣ ሰባት የሬዲዮ ጣቢያ ያለው በቅርቡ ደግሞ የሰቆጣ የሬዲዮ ጣቢያ ሲጨመር ዕድገቱን ከፍ እንደሚያደርግ እና በትንሹ እየጀመረ ቀስ እያለ እያደገ የሚሄድ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል። ዛሬ አሚኮ ሌላ የዕድገቱ መገለጫ የኾነ እና አሁን ላይ የደረሰበትን የዕድገት ምዕራፍ ሊገልጥ ነው፤ ልጆቹም ደስታቸውን እና መሠልጠናቸውን ለዓለም ሊገልጡ እየተዘጋጁ ነው።
የዓለማችን ትልልቅ የመገናኛ ብዙኀን እንደ አልጀዚራ፣ ፕሬስ ቲቪ፣ ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ አርቲቪ የየሀገራቸው መገለጫ እንደኾኑት ሁሉ አሚኮም አሁን በያዘው የዕድገት ጉዞ የሀገሩ ኢትዮጵያ መገለጫ መኾኑ አይቀሬ ነው፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የዛሬው ሁነት እና ደረጃው ማሳያ የሚኾን ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!